ኮሮናቫይረስ፡ ኡበር ውስጥ ጭምብል አላጠልቅም ያለችው ግለሰብ በፖሊስ ተያዘች

ታክሲ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ታትሟል

በአሜሪካ ሳንፍራንሲስኮ ከተማ ኡበር ታክሲ ውስጥ የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ጭምብል ለመልበስ ፈቃደኛ ካለመሆኗም በላይ ሾፌሩን በርበሬ በመርጨት ጥቃት የፈጸመችዋ ግለሰብ በቁጥጥር ስር ዋለች፡፡

የ24 ዓመቷ ማሌዢያ ኪንግ "የኬሚካል ጥቃትን" ጨምሮ በርካታ ክሶች እንደሚጠብቋት ፖሊስ አስታውቋል፡፡

ኪንግ መኪናው ውስጥ በተገጠመው ካሜራ ከተቀረጹት ሦስት ተሳፋሪዎች አንዷ ስትሆን ሌላኛዋ በሾፌሩ ላይ ስትስል ትታያለች፡፡

ሁለተኛዋ ተጠርጣሪ የ24 ዓመቷ አርና ኪሚያይ ራሷን አሳልፋ እንደምትሰጥ አሳውቃለች ብሏል ፖሊስ፡፡

የሳን ፍራንሲስኮ ፖሊስ መምሪያ ባልደረባ የሆኑት ትሬሲ ማክሬይ "ኪሚያይ ትክክለኛውን ነገር ለማድረግ እንዳሰበች መስማታችን አስደስቶናል። በፍጥነት እንደምታደርገው ተስፋ እናደርጋለን" ብለዋል፡፡

ፖሊስ እንዳስታወቀው ኪንግ ሐሙስ ዕለት በሎስ አንጀለስ ፖሊሶች ድጋፍ በቁጥጥር ስር ውላለች፡፡ ሌሎች የሚቀርቡባት ክሶች "ጥቃት" እና የከተማዋን የጤና እና ደህንነት ሕጎች መጣስ የሚሉ ናቸው፡፡

እሑድ መጋቢት 7 ከሰዓት በኋላ በተፈጠረው በዚሁ ጉዳይ ላይ ምርመራው እንደቀጠለም ተገልጿል፡፡

በ32 ዓመቱ የኡበር አሽከርካሪ ሱባካር ካድካ ከቀረቡት ክሶች መካከል ተሳፋሪዎቹ የአፍና አፍናጫ መሸፈኛ ጭምብል ለማድረግ አለመፍቀዳቸውን ያካተተ ነው።

ከተጠርጣሪዎች አንዷ የሞባይል ስልኩን ለመስረቅ የሞከረች ስትሆን፤ በርበሬ ለመርጨትም ሙከራ ተደርጎ ሊሆን እንደሚችል ፖሊስ ገልጿል፡፡

የኮቪድ -19 ስርጭትን ለመከላከል በሳን ፍራንሲስኮ ውስጥ ከሚተገበሩ ደንቦች መካከል የቤተሰብ አባል ካልሆነ ሰው በሁለት ሜትር መራቅ እና "የህዝብ ትራንስፖርት በሚጠቀሙበት ጊዜ አፍ እና አፍንጫን መሸፈን" የሚሉት ይገኙበታል፡፡

ቪዲዮው ምን ያሳያል?

በካድካ ተሽከርካሪ ላይ የተገጠመው ካሜራ የያዘው ምስል ሶስት ሴት ተሳፋሪዎችን ከኋላ ተቀምጠው ያሳያል። ከእነዚህም መካከል ሁለቱ በአንድ ጊዜ የፊት መሸፈኛዎቻቸውን ያወልቃሉ፡፡ ሦስተኛዋ ተሳፋሪ እስካሁን በስም አልተገለጸችም፡፡

ከመካከላቸው አንዷ ወደ ካድካ ዘንበል በማለት የምትስል ይመስላል፡፡ ፊት ለፊት የሚገኘውን የሞባይል ስልክ ልትነካ ስትሞክር "ንብረቴን አትንኩ" የሚል ምላሽ ይሰጣል።

ይህችው ግለሰብ የካድካን የፊት መሸፈኛ ጭምብል በማውለቅ "ወደ ማንፈልገው ቦታ እየወሰድከን ነው" በማለት ትከሳለች፡፡

ካድካ ጉዳዩን ሪፖርት ባደረጉበት ወቅት ከተሳፋሪዎቻቸው አንዷ ጭምብል እንደሌላት ካወቁ በኋላ ማሽከርከር እንዳቆሙ ለፖሊስ ተናግረዋል፡፡

የፊት መሸፈኛዎቻቸውን በትክክል እስኪያደርጉ ድረስ ማሽከርከር እንደማይችል ሲነግራቸው "ጠብ" ተከስቷል ብሏል፡፡

ሦስቱ መንገደኞች ከተሽከርካሪው ሲወጡ አንደኛዋ "በተከፈተው መስኮት በኩል በርበሬ ተብሎ የተገመተ ነገር ወደ አሽከርካሪው ረጭታለች" ሲል ፖሊስ አስታውቋል፡፡

በካሜራ ላይ የተቀረፀው ባህሪ ወረርሽኝ በመካከል ወቅት አስፈላጊ አገልግሎት ሰጭ ሠራተኛን ደህንነት ላይ ቸልተኝነት መኖሩን እንደሚያሳይ ፖሊስ በድረ ገጹ ባወጣው መግለጫ አመልክቷል።

መግለጫው አክሎም "በሳን ፍራንሲስኮ ይህን ጉዳይ በቁም ነገር እንመለከተዋለን። በዚህ ጉዳይ ላይ ፍትህ እንዲሰጥ ለማድረግ እንደምንሠራ ቃል እንገባለን" ብሏል፡፡