ኮቪድ-19፡ ጣሊያን የወረርሽኙ ሥርጭት በመጨመሩ ሱቆችንና ትምህርት ቤቶችን ልትዘጋ ነው

ሰዎች በጣሊያን ሮም ከተማ ሲንቀሳቀሱ

የፎቶው ባለመብት, EPA

ታትሟል

በዓለማችን ወረርሽኙ እንደተከሰተ ከሌሎች አራት ቀድማ በርካታ ዜጎቿን ባጣችው ጣሊያን፤ አሁንም የቫይረሱ ሥርጭት አልተገታም።

በዚህም ምክንያት ሱቆች፣ ምግብ ቤቶች እና ትምህርት ቤቶች በበርካታ የአገሪቷ ክፍሎች ከሰኞ ጀምሮ እንደሚዘጉ ጠቅላይ ሚኒስትር ማሪዮ ድራጊ አስታውቀዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ አዲስ ዙር የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ እንደሚያጋጥምም አስጠንቅቀዋል።

በፋሲካ በዓል አካባቢ ባሉት ሦስት ቀናትም ሙሉ በሙሉ የእንቅስቃሴ ገደብ ይጣላል ተብሏል።

በአዲሱ የእንቅስቃሴ ገደብ ሕዝብ የሚበዛባቸውን ሮምና ሚላንን ጨምሮ በግማሹ የጣሊያን ክፍል ትምህርት ቤቶች፣ ሱቆችና እና ምግብ ቤቶች ከሰኞ ጀምሮ ዝግ ይሆናሉ።

በመሆኑም ነዋሪዎች ከሥራ፣ ጤና ወይም ከሌላ አንገብጋቢ ጉዳይ ከሌላቸው በስተቀር ቤታቸው ውስጥ እንዲቆዩ ይገደዳሉ።

እነዚህ ገደቦች እስከ ፋሲካ ድረስ እንደሚቆዩም የጠቅላይ ሚኒስተር ጽህፈት ቤት አስታውቋል።

ይህ መሆኑ በልጆች ትምህርት እና ኢኮኖሚ ላይ ተፅእኖ የሚያደርግ ቢሆንም ሥርጭቱን ለመግታት ግን ግድ ነው ብለዋል- ጠቅላይ ሚኒስትሩ።

ጣሊያን የመጀመሪያውን የእንቅስቃሴ ገደብ የጣለችው ከአንድ ዓመት በፊት ነበር፤ ነገር ግን አሁንም የቫይረሱን ሥርጭት ለመግታት እየታገለች ነው።

እስካሁን አገሪቷ ከኮቪድ-19 ጋር በተያያዘ ከ100 ሺህ በላይ ሰዎችን በሞት አጥታለች። በዚህ በአውሮፓ ካሉ አገራት ከዩናይትድ ኪንግደም ቀጥላ ከፍተኛ ሞት የተመዘገበባት አገር ሆናለች።

በጣሊያን ባለፈው ዓመት ወረርሽኙ ከተከሰተ አንስቶ 3.2 ሚሊዮን ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸው ተረጋግጧል።

ይሁን እንጅ በሌሎች የአውሮፓ ሕብረት አባል አገራት እንደታየው በጣሊያንም የክትባት ዘመቻዎች መዘግየት አጋጥሞታል።

ባለፈው ሳምንት የጣሊያን መንግሥት የክትባት እጥረትን ለመቀነስ 250 ሺህ ብልቃጥ የኦክስፎርዱን አስትራዜኔካ ክትባት ወደ አውስትራሊያ እንዳይላክ አግዶ ነበር።

በሌላ በኩል በቡልጋሪያ፣ ዴንማርክ እና ኖርዌይ የኦክስፎርዱን አስትራዜኔካ ክትባት የደም መርጋት ያስከትላል በሚል ስጋት መጠቀም አቁመዋል።

ይሁን እንጅ የዓለም ጤና ድርጅት አርብ ዕለት ይህ እውነት መሆኑን የሚያረጋገጥ ማስረጃ እንደሌለ አስታውቋል።

ድርጅቱ አገራቱ ክትባቱን መጠቀም ማቆም እንደሌለባቸውም በአፅንኦት አሳስቧል።

በሌሎች የአውሮፓ አገራትስ የወርርሽኙ ሥርጭት ምን ይመስላል?

ፖላንድ፡ አርብ ዕለት ብቻ በአንድ ቀን 19 ሺህ የሚሆኑ አዲስ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎችን መዝግባለች። ይህም ከኅዳር ወዲህ የተመዘገበ ከፍተኛው ቁጥር ነው ተብሏል።

ጀርመን፡ ጀርመንም በቫይረሱ የሚያዙ ተማሪዎች ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ ነው። ይህም አዲሱ የቫይረስ ዝርያ እንደሆነ ይነገራል።

ፈረንሳይ: በጽኑ ህሙማን ክፍል የገቡ ታማሚዎች ቁጥር ከ4 ሺህ በልጧል። ይህ ቁጥር በሦስት ወራት ውስጥ የተመዘገበ ከፍተኛ ቁጥር ነው ተብሏል። ይሁን እንጂ መንግሥት ተጨማሪ የእንቅስቃሴ ገደቦችን አልጣለም።

ስሎቫኪያ እና ቼክ ሪፐብሊክ፡ እነዚህ አገራት ከአውሮፓ ሕብረት ውጭ ተቀባይነት ያገኙ ክትባቶችን በመግዛት መንግሥታቸው ቀውስ ውስጥ ገብቷል።