ጆርጅ ፍሎይድ ፡ ሚኒያፖሊስ በፖሊስ ለተገደለው ለጆርጅ ፍሎይድ ቤተሰብ 27 ሚሊዮን ዶላር ሊከፍል ነው

ጆርጅ ፍሎይድ

የፎቶው ባለመብት, TWITTER/RUTH RICHARDSON

የምስሉ መግለጫ, ጆርጅ ፍሎይድ
ታትሟል

የአሜሪካዋ ሚኒያፖሊስ ከተማ ባለፈው ዓመት ግንቦት ወር ግድያውን ተከትሎ በዓለም ዙሪያ ተቃውሞ ላስነሳው ጥቁር አሜሪካዊ ጆርጅ ፍሎይድ ቤተሰቦች 27 ሚሊዮን ዶላር ለመክፈል ከስምምነት ደረሰ።

ፍሎይድ ነጩ የፖሊስ መኮንን ዴሪክ ቾቪን መሬት ላይ ተጥሎ አንገቱ ላይ በጉልበቱ ቆሞ ለሞት ሲያበቃው የሚያሳየው የጭካኔ ድርጊት በካሜራ ተቀርጾ በአሜሪካና በዓለም ዙሪያ ከባድ ቁጣን ቀስቅሶ ነበር።

ለቤተሰቡ ጠበቆች ቪዲዮው "የማይካድ የፍትህ እና የለውጥ ፍላጎት" እንደፈጠረ ተናግረዋል።

ግድያውን ፈጽሟል ተብሎ የተጠረጠረውን የፖሊስ መኮንን ጉዳይ የሚመለከቱ ዳኞች ምርጫ በመካሄድ ላይ ነው።

በቅርቡ ለሚሰየመው ችሎት ከሚያስፈልጉ 12 ዳኞች መካከል ስድስቱ እስካሁን ተመርጠዋል።

የሚኒያፖሊስ ከተማ ምክር ቤት በሚኒሶታ ግዛት ታሪክ ትልቁ የተባለውን የቅድመ-ፍርድ ካሣን ለመክፈል በሙሉ ድምፅ አፀደቋል።

የፍሎይድ የቤተሰብ ጠበቃ ቤን ክረምፕ "ለግድያ የተሰጠው ትልቁ ካሣ ለጥቁር ሰው ሕይወት መሆኑ ጠንከር ያለ መልዕክት ያስተላልፋል። ፖሊስ በጥቁሮች ላይ ጭካኔ በተሞላበት መንገድ የሚወስዳቸው እርምጃዎች መቆም አለባቸው" ብለዋል።

በማኅበራዊ ሚዲያዎች ላይ በተሰራጨውና የፍሎይድን ሞት በሚያሳየው ዘግናኝ ቪዲዮ ላይ አራት የፖሊስ መኮንኖች ግለሰቡን በአንድ ሱቅ ውስጥ ሐሰተኛ 20 ዶላር ተጠቅመሃል በሚል ግብግብ ገጥመውታል።

ከዚያም መሬት ላይ ጥለው የጎተቱት ሲሆን ቾቪን ደግሞ ጉልበቱን ፍሎይድ አንገት ላይ በማድረግ ተንበርክኮበታል። በህይወት ለመቆየት "መተንፈስ አልቻልኩም" በማለት ሲማጸንም የተሰማ ሲሆን በኋላም መሞቱ ተነግሯል።

የፍሎይድ ቤተሰብ ጠበቆች ከግድያው ከአንድ ወር በኋላ ባለፈው ዓመት ሰኔ ላይ የፍትሐ ብሔር ክስ መስርተዋል።

ከተማዋ ባለሥልጣናት ፖሊሶችን በተገቢው መንገድ ማሠልጠን ባለመቻላቸው እና ኃላፊነታቸውን በአግባቡ ባለመወጣታቸው ቸልተኛ ናቸው ሲሉ ተከራክረዋል።

በከተማው የፖሊስ ኃይል ውስጥ ለ 19 ዓመታት ያገለገለው ዴሪክ ቾቪን ላይ በደርዘን የሚቆጠሩ ቅሬታዎች ቀርበዋል።

ከካሣው በኋላ ሃሳባቸውን የተናገሩት ጠበቃ ክረምፕ ይህ ወደ ፍትህ በሚደረገው ጉዞ አንድ እርምጃ ነው ብለዋል። የፍሎይድ መገደል በዘር እና በአድሎአዊነት በሚፈጸሙ ጉዳዮች ላይ መነሻ ነበር ብለዋል።

የቀድሞው የፖሊስ መኮንን በግድያ ወንጀል ተከሷል። በሁሉም ክሶች ጥፋተኛ ሆኖ ከተገኘ በ65 ዓመት እስራት ሊቀጣ ይችላል። ሆኖም ግን ተጠርጣሪው ጥፋተኛ አይደለሁም ብሏል።

ጉዳዩን ለሚመለከተው ችሎት እስካሁን ስድስት የሕግ ባለሙያዎች ተመርጠዋል።

12 ዳኞችን እና አራት ተለዋጭ ወይም ተተኪዎችን ይፈልጋሉ። ለዚህ በስሜት ለተሞላና በከፍተኛ ደረጃ ትኩረትን ለሳበ ጉዳይ ተስማሚ ዳኞችን ማግኘት አስቸጋሪ ሆኗል።

በፍሎይድ ሞት የተሳተፉ ሌሎች ሦስት መኮንኖች ጄ አሌክሳንደር ኬንግ፣ ቱ ታኦ እና ቶማስ ሌን ደግሞ ግድያውን በመደገፍ ወንጀል የተከሰሱ ሲሆን ለብቻቸው ተለይተው ለፍርድ ይቀርባሉ።