ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የግብጹ ኮከብ ስሙን ከሽብር ተጠርጣሪዎች ዝርዝር ለማስወጣት ሳይችል ቀረ
የቀድሞው የግብጽ ብሔራዊ ቡድን ተጫዋች ሞሐመድ አቡትሪካ ከሽብር ጋር በተያያዘ ክትትል ከሚደረግባቸው ሰዎች ዝርዝር ውስጥ ስሙ እንዲወጣ የጠየቀው ይግባኝ ውድቅ ተደረገበት።
በግብጽ እግር ኳስ ውስጥ ምርጥ ከሚባሉት ተጫዋቾች መካከል አንዱ የሆነው አቡትሪካ ከዚህ በፊትም ተመሳሳይ ጥያቄ አቅርቦ ተቀባይነት ሳያገኝ ቀርቶ ነበር።
ሞሐመድ አቡትሪካ በእግር ኳስ ካለው ድንቅ ብቃት በተጨማሪ በፖለቲካው መስክም ባለው ሚና ስሙ ይጠቀሳል።
አቡትሪካ የዛሬ አስር ዓመት ለሆስኒ ሙባረክ ከስልጣን መወገድ ምክንያት በሆነው ሕዝባዊ ተቃውሞ ውስጥ ጉልህ ሚና ነበረው።
ነገር ግን ሙባረክ ከስልጣን ተወግደው በግብጽ በተካሄደ የመጀመሪያው ዲሞክራሲያዊ ምርጫ ተመርጠው ፕሬዝዳንት የሆኑት ሞሐመድ ሞርሲ ከስልጣን በኃይል ሲወገዱ ቡድናቸው "ሙስሊም ወንድማማችነት" ሕገ ወጥ ተደርጓል።
በዚህም ሞሐመድ አቡትሪካ ከዚሁ ቡድን ጋር ግንኙነት አለው በሚል ተከሶ ነበር።
በተጨማሪም አንዳንድ ንብረቶቹ በመንግሥት ቁጥጥር ስር እንዲውሉ ተደርገው ከሽብር ጋር ተያይዞ ክትትል ከሚደረግባቸው ሰዎች ዝርዝር ውስጥ ከሦስት ዓመት በፊት እንዲገባ ተደርጓል።
አቡትሪካ ኑሮውን በኳታር ያደረገ ሲሆን እዚያም በጣም ስኬታማ የሆነ የእግር ኳስ ተንታኝ በመሆን ከስፖርቱ ሳይርቅ በመስራት ላይ ነው።
አቡትሪካ በአፍሪካ እግር ኳስ ውስጥ በቀዳሚነት ከሚጠቀሱት አገራት አንዷ በሆነችው ግብጽ ውስጥ በአጥቂ መስመር ዝናን ካተረፉ ተጫዋቾች መካከል በቀዳሚነት ይጠቀሳል።
ለተለያዩ የእግር ኳስ ሽልማቶች በተለያዩ ጊዜያት በእጩነት ቀርቦ የነበረው አቡትሪካ በ2008 (እአአ) ከኢማኑኤል አዲባዮር ቀጥሎ የዓመቱ የአፍሪካ ኮከብ እግር ኳስ ተጫዋች ተብሎ ነበር።
በእግር ኳስ ተጫዋችነት ዘመኑ ከአገሩ ብሔራዊ ቡድን ጋር የአፍሪካ ዋንጫን ያነሳ ሲሆን፤ ከቡድኑ አል አልህሊ ጋርም በታላላቅ ውድድሮች ላይ ተጫውቷል።