ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ኮሮናቫይረስ፡ የኬንያ ተቃዋሚ ፓርቲ መሪ ራይላ ኦዲንጋ በኮቪድ-19 ተይዘዋል ተባለ
የኬንያ ተቃዋሚ ፓርቲ መሪ ራይላ ኦዲንጋ በትናንትናው እለት በኮሮናቫይረስ መያዛቸውን ተከትሎ በለይቶ ማቆያ ውስጥ ናቸው ተብሏል።
ራይላ ኦዲንጋ ድካም ተሰምቷቸው በመዲናዋ ናይሮቢ ወደሚገኝ ሆስፒታል የተወሰዱት በያዝነው ማክሰኞ እንደሆነ ቢቢሲ ከቤተሰባቸው መረዳት ተችሏል።
ሆስፒታል ደርሰው ምርመራ ከተደረገላቸው በኋላ ኮሮናቫይረስ መሆኑም ታውቋል።
"በአሁኑ ወቅት ህክምና እየተደረገላቸው ነው፤ ጥሩ ጤንነትም ላይ ይገኛሉ። ከቀን ወደ ቀን የሚያሳዩትንም ለውጥ በቅርበት የምንከታተል ይሆናል" በማለት ዶክተራቸው ባወጡት መግለጫ አሳውቀዋል።
ራይላ ኦዲንጋም ቢሆኑ ከዶክተሩ በኋላ የራሳቸውን መግለጫ ያወጡ ሲሆን "በአሁኑ ወቅት በጥንካሬና በመልካም ጤንነት እገኛለሁ" ብለዋል።
ነገር ግን በዶክተሮቻቸው ምክር መሰረት አስገዳጅ በሆነ ለይቶ ማቆያ ውስጥ እንደሚቆዩም ተናግረዋል።
የአገሪቱ ጤና ሚኒስቴር እንዳስታወቀው ኬንያ ሶስተኛ ዙር የተባለውን የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ማገርሸት እያስተናገደች ነው።
በያዝነው ሃሙስ አገሪቷ 829 አዲስ ህመምተኞችን የመዘገበች ሲሆን ከጥር በኋላ ትልቁ ቁጥር ነው ተብሏል።
የ76 አመቱ ፖለቲከኛው ራይላ ኦዲንጋ በአገሪቱ ውስጥ በባለፉት ወራት ከፍተኛ ቅስቀሳዎችን ሲያካሂዱ ከነበሩ ፖለቲከኞች መካከል ይጠቀሳሉ።
ምንም እንኳን አገሪቷ ስብሰባን አስመልክቶ ጠበቅ ያለ የኮሮናቫይረስ መመሪያ ቢኖራትም ራይላ መመሪያዎቹን ብዙ ከግምት ውስጥ አላስገቧቸውም ተብሏል።