በፈረንሳይ አንገቱን ተቀልቶ የተገደለው መምህር የተነዛበት መረጃ ሃሰት ነው ተባለ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በፈረንሳይ አንገቱን ተቀልቶ የተገደለው መምህር ጋር በተያያዘ የወጣው መረጃ ሃሰትና ሆን ተብሎም እንደተነዛ ከሰሞኑ አንዲት ተማሪ ተናግራለች።
ተማሪዋ የሃሰት መረጃውን እንደነዛችም አምናለች።
በጥቅምት ወር ላይ አንገቱን ተቀልቶ የተገደለው ሳሙኤል ፓቲ ተማሪዎቹን የነብዩ መሃመድን የካርቱን ምስል አሳይቷል መባሉን ተከትሎ ነው።
ተማሪዋ የነብዩ መሃመድ ካርቱን ምስል ያሳያል ማለቷን ተከትሎ ከፍተኛ ዘመቻ በመምህሩ ላይ ተከፍቶበት ነበር። ሆኖም ሃሰት እንደሆነና በወቅቱም በመማሪያ ክፍሉ እንዳልነበረች አምናለች።
የመምህሩ ግድያ መላ ፈረንሳይን ያስደነገጠ ሲሆን በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች በመላው አገሪቷ በሚገኙ ከተሞች ዘክረውታል።
ስሟ ያልተጠቀሰው የ13 አመቷ ታዳጊ በመጀመሪያ ለአባቷ እንደተናገረችው መምህሩ ሙስሊም ተማሪዎች እንዲወጡና የነብዩ መሃመድ ካርቱንን በማሳየት ሃሳብን በነፃነት የመግለፅ መብትንና እምነቱንም የሚያንቋሽሽ ነገር ይናገር ነበር ብላለች።
"ታዳጊዋ መውጣት የማትችልበት ወጥመድ ውስጥ እንደገባች ስለተሰማትና የክፍሏ ተማሪዎችም ቃለ አቀባይ እንድትሆን ስለጠየቋት ነው" በማለት የተማሪዋ ጠበቃ ምቤኮ ታቡላ ለአጃንስ ፍራንስ ፕሬስ የዜና ወኪል ተናግረዋል።
የታዳጊዋ አባት በመምህሩ ላይ ክስ ከመፈት በተጨማሪ በበይነ መረብ ላይ የጥላቻ ዘመቻ ከፍተውበት ነበር ተብሏል።
አቃቤ ህግ ከመምህሩ ግድያ በኋላ በሰጠው መግለጫ "በፓቲ ላይ የተከፈተበት ዘመቻና ግድያው በቀጥታ ግንኙነት አላቸው" ብሏል።
በሌላ ቋንቋ ለመምህሩ ግድያ መነሻ የሆነው በበይነ መረብ የተከፈተበት ዘመቻ ነው።
ግድያውን ፈፅሟል የተባለው የ18 አመቱ አብዱላክ አንዞሮቭ ከጥቃቱ በኋላ በፖሊስ በጥይት ተገድሏል።
ታዳጊዋ ተማሪ በስም ማጥፋት ዘመቻ የተከሰሰች ሲሆን የእስልምና መምህር የሆኑት አባቷ ደግሞ ከግድያው ጋር በተያያዘ ክስ ቀርቦባቸዋል።
የአገሪቱ ፕሬዚዳንት ኢማኑኤል ማክሮን አገራቸው የምትሰጠውን ከፍተኛ ማዕረግ ሽልማት ሌጊዮን ዲ ሆነር ለመምህሩ ቤተሰቦች ሰጥተዋል።
የነብዩ መሃመድ ምስል በማንኛውም መንገድ ማሳየት በእስልምና ዘንድ የተወገዘና አፀያፊ ነው።
በተለይም ይህ ሁኔታ አወዛጋቢ የሆነው የፈረንሳዩ የቧልት መፅሄት ቻርሊ ሄብዶ የነብዩ መሃመድን ካርቱን ማተሙን ተከትሎ ነው፥
ከዚህም ጋር በተያያዘ በ2015 በመፅሄቱ ቢሮ በደረሰ ጥቃት አስራ ሁለት ሰዎች መገደላቸው ይታወሳል።












