የጆርጅ ፍሎይድን ግድያ ለመመርመር ዳኞች እንዴት ይመረጣሉ?

ታትሟል

ጆርጅ ፍሎይድ ህይወቱ ከማለፉ በፊት ዴሪክ ቼቪን ለዘጠኝ ደቂቃዎች ያህል አንገቱን በጉልበቱ ተጭኖ የሚያሳየው ቪዲዮ በመላው ዓለም ታይቷል።

ይህን ተከለትሎ የቀድሞው የአሜሪካ ፖሊስ መኮንን በሁለተኛ ደረጃ ወንጀል ተከስሷል።

ሦስት የተባረሩ መኮንኖችም በዚህ ዓመት አብረውት ለፍርድ ይቀርባሉ። የቻውቪን ችሎት የሚከታተሉ ዳኞች ምርጫ ሰኞ ይጀምራል።

ዳኞቹ እንዴት ይመረጣሉ?

መስፈርቶችን የሚያሟሉ በሚኒሶታ በሄኔፒን ካውንቲ የሚኖሩ ሰዎች ተጋብዘዋል። ከእነሱ ውስጥ 12 ዳኞች እና አራት ተለዋጭ ዳኞች ይመረጣሉ።

እጩ ዳኞቹ ዴሪክ ቻውቪንን ጉዳይ በትክክል ይከታተሉ እንደሆነ ጥያቄዎች ይቀርቡላቸዋል። እያንዳንዳቸውም ጉዳዩን ስለማወቃቸው፣ ስለዜና ልምዶቻቸው እና ከህግ አስከባሪ አካላት ጋር ስላላቸው ግንኙነት የሚጠይቅ ባለ 16 ገጽ መጠይቅ ደርሷቸዋል፡፡

ከእነዚህም መካከል የጆርጅ ፍሎይድ ሞትን የሚያሳየውን ቪዲዮ ምን ያህል ጊዜ እንደተመለከቱ እና ይህንን ተከትሎ በተቀሰቀሱ የተቃውሞ ሰልፎች ወቅት ተሳትፈው እንደሆነ ወይም ንብረታቸው ላይ ጉዳት ደርሶ እንደሆነ የሚጠይቁ ቀጥተኛ ጥያቄዎችን ያካትታል።

ከሰኞ ጀምሮ አራት ሊሆኑ የሚችሉ ዕጩ ዳኞች ጠዋት እና ከሰዓት በኋላ ቀርበው ብቁነታቸውን ለመገምገም በተናጠል ይጠየቃሉ።

ዓቃቤ ሕግ እና መከላከያ ፒተር ካሂል የተባሉት ዳኛ በጥያቄ ወቅት አድልዎ ወይም የጥቅም ግጭትን ከተመለከቱ "በምክንያትነት ጠቅሰው" እንዲሰናበቱ መጠየቅ ይችላሉ፡፡

እንዲሁም አንድን ሰው ያለምንም ምክንያት ከዕጩዎች ውስጥ ለማስወጣት ውስን "ፈተናዎች" ማቅረብ ይችላሉ። ከእነዚህ ውስጥ ዓቃቤ ሕግ ዘጠኝ የቻውቪን የመከላከያ ቡድን አባላት ደግሞ 15 አላቸው።

በሁለቱም ወገኖች አንድ ሰው በጾታ ወይም በዘር በመሳሰሉ ምክንያቶች መድልዎ እንደደረሰበት ከጠረጠሩ መባረራቸውን ሊቃወሙ ይችላሉ።

16ቱ ሰዎች ከፀደቁ በኋላ ዳኞቹ ችሎት ሊቀመጡ ይችላሉ፡፡ ይህ ሂደት ሳምንታትን ሊወስድ የሚችል ሲሆን ችሎቱም ከፈረንጆቹ መጋቢት 29 2021 እንደማይጀምር ቀድሞውንም ይታወቃል።

ይህ ሂደት ከእንግሊዝ እንዴት ይለያል?

በዳኞች የመዳኘት መብት በአሜሪካ ህገ-መንግስት የተረጋገጠ ነው፡፡ በእንግሊዝ እና በዌልስ ይህ ብዙም የተለመደ አይደለም።

በዩናይትድ ኪንግደም ዳኞች በዘፈቀደ ተመርጠው ቅድመ-ውሳኔን ለማስወገድ ቃለ መሃላ እስኪፈጽሙ ድረስ በየትኛው የፍርድ ሂደት እንደሚያገለግሉ አያውቁም፡፡ በተጨማሪም በእንግሊዝ ፕሬስ ውስጥ ተጠርጣሪዎች ፍትሃዊ ፍርድ እንዲያገኙ ለማድረግ በጣም ጥብቅ የዘገባ ገደቦች አሉ፡፡

ብቁ የሆኑት እጩዎች መስቀለኛ ጥያቄ ባይቀርብባቸውም ተበዳይን እንደማወቅ ባሉ ልዩ ሁኔታዎች ዳኛው ብቻውን ማሰናበት ይችላል፡፡ በንድፈ ሀሳብ ደረጃ ሁሉም ወንዶች ወይም ሴቶች ብቻ የሆኑበት የዳኞች ምርጫ እንዲኖር ማድረግ ይቻል ይሆናል፡፡

የአሜሪካ የመመዘኛ ስርዓት ብዙ የህብረተሰብ ክፍሎች መወከላቸውን ለማረጋገጥ የበለጠ ትኩረት ይሰጣል፡፡ እንደ ዘረኝነት ያሉ ጉዳዮች ላይ የምርጫው ሂደት ለችሎቱ ውጤት እና ለፍትሃዊነት ሲባል አካሄዱ እጅግ አስፈላጊ እንደሆነ ተደርጎ ሊታይ ይችላል።

ከፍተኛ ትኩረት ያላቸው የዩናይትድ ስቴትስ የዳኝነት ሂደቶች የሕግ ባለሙያዎች ምርምር እንዲያደርጉ እና ዳኞች እንዲመረጡ የሚረዱ ልዩ አማካሪዎችን የሚያካትቱ በመሆናቸውም ጥሩ ውጤት ለማግኘት ይሞክራሉ። የዳኞች ዳራ እና የሰውነት ቋንቋቸው ጭምር በሂደቱ ሊታሰቡ ይችላሉ።

በቻውቪን የፍርድ ሂደት ወቅት ዳኞች ለተወሰነ ጊዜ ይደበቃሉ ወይም ይገለላሉ። ዋናው ሂደት ከተጀመረ በኋላ ሙሉ በሙሉ ይደበቃሉ፡፡ በተጨማሪም ዳኛው ማንነታቸውን ለህዝብ ይፋ ለማድረግ እስከሚፈቅድ ድረስ ማንነታቸው አይገለጽም፡፡

የአሜሪካ ዳኞች ከዚያ በኋላ ስለሂደቱ መናገሩ የተለመደ ነገር ነው። እንደ ኦጄ ሲምሰን ባሉ የፍርድ ሂደቶች ውስጥ ደግሞ አንዳንዶቹ ልምዶቻቸው በተመለከተ መጽሐፍትን እስከ መጻፍ ደርሰዋል፡፡

ዳኞችን በመምረጥ ሂደት ምን ችግሮች አሉ?

የጆርጅ ፍሎይድ ሞት በዓለም ዙሪያ በዘር ላይ የሚፈጸመውን ኢ-ፍትሃዊነት የሚቃወሙ እንቅስቃሴዎችን ለሳምንታት ቀስቅሷል፡፡

ብዙዎች ችሎቱን በቅርብ የሚከታተሉ ሲሆን የአካባቢው ባለስልጣናት ከችሎቱ በፊት በፍርድ ቤቱ እና በሌሎች የመንግሥት ሕንፃዎች ዙሪያ ጥበቃውን አጠናክረዋል፡፡

በሕዝብ ዘንድ ካለው ማስረጃ አንጻር የቻውቪን የፍርድ ሂደት በዘር ላይ ለተመሠረተ ክስ እና ከሕግ አስከባሪዎች ቸልተኛነት ጋር በተያያዘ ለአሜሪካ የፍትሕ ሥርዓት እውነተኛ ፈተና ተደርጎ ይወሰዳል።

የፍሎይድን ሞት የማያውቁ ዳኞችን ማግኘት የማይታሰብ ነው። እያንዳንዳቸውም በፍትሃዊነት እና ገለልተኛ በሆነ መንገድ ለመወሰን የቀድሞ አመለካከቶቻቸውን ወደ ጎን ይሉ እንደሆነ ተጠይቀዋል፡፡

በኮርኔል የሕግ ትምህርት ቤት ተመራማሪ የሆኑት ፕሮፌሰር ቫለሪ ሃንስ እንደሚሉት በዚህ ጉዳይ ላይ የቅድመ-ምርመራ መጠይቁ የበለጠ ዝርዝር እና ግላዊ ነው፡፡

በሌሎች ጉዳዮች ላይ ባለሙያዎቹ የሚያውቁት የጋብቻ ሁኔታን እና የሙያ መረጃን የመሳሰሉ መሰረታዊ ነገሮችን ብቻ ይሆናል ይላሉ። በቻውቪን ጉዳይ ግን "ስለወቅታዊው ፖለቲካዊ እና ማህበራዊ ርዕሰ ጉዳዮች ጥልቅ አመለካከታቸው" ተጠይቀዋል ብለዋል፡፡

በማሳያነትም ብላክ ላይቭስ ማተር እና ብሉ ላይቭስ ማተር ላይ ስላላቸው ሃሳብ መጠየቃቸውን አንስተዋል። እነዚህን አመለካከቶች ማወቅ ዳኞች እንዴት ማስረጃዎችን እንደሚመለከቱ ለመተንበይ ከሌሎች መስፈርቶች የተሻሉ ጠቋሚዎች ሊሆኑ ይችላሉ ይላሉ፡፡

ምርጫ ውስጥ የዘር ጉዳይ አንድ አካል ይሆናልን?

ለጥያቄዎቹ የሚሰጡ ምላሾች ሁኔታ ለሁለቱም ወገኖች በፍትሃዊነት ላይ ተቃውሞዎችን ለማንሳት ዕድል ይሰጣቸዋል፡፡

"እያንዳንዱ ወገን ይህንን መጠይቅ ሙሉ በሙሉ እየሞላ ከሆነ በአንጻራዊ ሁኔታ ለእነሱ ምቹ ዳኛ ይሆናል ብለው ስለሚያስቡ እና ምናልባትም ሌላኛው ወገን ላይቀበላቸው የሚፈልግ ዓይነት ስሜት ይኖረዋል፡፡"

"እኔ እንደማስበው ስለፖሊስ ያላቸው አመለካከት በዘር ይለያያል። እናም የብዙ ዳኞች ምርጫ ጥያቄዎች ስለፖሊስ ፍትሃዊነት አመለካከቶችን እና ስሜትን ያካተቱ በመሆናቸው ማምለጥ አይቻልም" ሲሉ የዘር ጉዳይ የምርጫው አንድ አካል ሊሆን ይችላል ወይ ለሚለው ጥያቄ ምላሽ ይሰጣሉ።