ብሪታኒያ ከናይጄሪያ በአንድ ባለስልጣን የተዘረፈን ገንዘብ ልትመልስ ነው

ታትሟል

የናይጄሪያ አንድ ግዛት የቀድሞ አስተዳዳሪ በነበረ ግለሰብ የተዘረፈን በሚሊዮኖች የሚቆጠር ዶላር ለመመለስ ዩናይትድ ኪንግደም ቃል ገባች።

ይመለሳል የተባለው ገንዘብ 5.8 ሚሊዮን ዶላር እንደሆነ ተነግሯል።

ዴልታ የምትባለው የናይጄሪያ ግዛት የቀድሞ አስተዳዳሪ የሆነው ጄምስ ኢቦሪ ዩናይትድ ኪንግደም ውስጥ ሕገ ወጥ የሆነ መንገድ የተገኘን ገንዘብ ሕጋዊ በማድረግ ወንጀል ከስምንት ዓመት በፊት ተከስሶ ተፈርዶበታል።

ግለሰቡ በነዳጅ ማዕድን ምርት ሀብታም ከሆነችው ግዛት 50 ሚሊዮን ፓውንድ የሚደርስ ገንዘብ ዘርፏል ተብሎ ይገመታል።

ዩናይትድ ኪንግደምና ናይጄሪያ በሕገ ወጥ መንገድና በወንጀለኞች ተዘረፈ ገንዘብን ለመመለስ ከአራት ዓመት በፊት ስምምነት ላይ ከደረሱ ወዲህ አሁን ይመለሳል የተባለው ገንዘብ የመጀመሪያው እንደሚሆን ባለስልጣናት ተናግረዋል።

የሁለቱ አገራት ዛሬ በተፈራረሙት ስምምነት መሠረት በዩናይትድ ኪንግደም ተቋማት አማካኝነት ተይዞ ወደ ናይጄሪያ ይመለሳል የተባለ 4.2 ሚሊዮን ፓውንድ መንገድን የመሳሰሉ የመሰረተ ልማቶች ግንባታ ላይ ይውላሉ ተብሏል።

ወደ ስድስት ሚሊዮን ዶላር የሚጠጋ ገንዘብ ተይዞበት ለናይጄሪያ መንግሥት እንደሚመለስ ተነገረው የቀድሞው የግዛት አስተዳዳሪ ጄምስ ኢቦሪ ከተራ ማጭበርበር ተነስቶ ለስልጣን የበቃና በሕገወጥ የገንዘብ ዝውውር የተፈረደበት ወንጀለኛ ነው ተብሏል።

ጄምስ እአአ በ1980ዎቹ ወደ ዩናይትድ ኪንግደም በመሄድ ለንደን ውስጥ በአንድ መደብር ውስጥ በገንዘብ ተቀባይነት ሲሰራ ገንዘብ ሰርቋል ተብሎ ቅጣት ተጥሎበት ነበር።

ከዚያ በኋላ ወደ አገሩ ናይጄሪያ ተመልሶ በፖለቲካ ውስጥ በመሳተፍ የአገሪቱ ሀብታም ግዛት አስተዳዳሪ እስከመሆን ደርሶ ነበር።

ግለሰቡ ለዴልታ ግዛት አስተዳዳሪነት በሚወዳደርበት ጊዜ የትውልድ ዘመኑን በተመለከተ ሐሰተኛ መረጃ እንደሰጠ ይነገራል። ይህንን ያደረገውም ዩናይትድ ኪንግደም ውስጥ የፈጸመውን ወንጀል ለመደበቅ ሲሆን ጥፋቱ ቢታወቅ ኖሮ ለምርጫ መወዳደር አይፈቀድለትም ነበር።

ጄምስ ለምርጫ ቀርቦ የዛሬ 20 ዓመት ገደማ ናይጄሪያ ከምታመርተው አብዛኛውን ነዳጅ ዘይት የምታገኝበትን የዴልታ ግዛት አስተዳዳሪ በሆነ በአጭር ጊዜ ውስጥ ከግዛቲቱ ካዝና ገንዘብ መውሰድ እንደጀመረ ይነገራል።

ከዚያም ለንደን ባለው ወኪሉ አማካኝነት የግል ጀት ለመግዛት ትዕዛዝ ከሰጠ በኋላ በ2005 (እአአ) የብሪታኒያ ፖሊስ በድጋሚ ግለሰቡን መከታተል ጀመረ።

ግለሰቡን ናይጄሪያ ውስጥ ለመያዝ ጥረት ቢደረግም ደጋፊዎቹ ፖሊሶች ላይ ጥቃት በመፈጸማቸው ለማምለጥ ችሏል። በመጨረሻም ከአስር ዓመት በፊት ዱባይ ውስጥ ተይዞ ለብሪታኒያ ተላልፎ ተሰጥቷል።