የፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ውሾች ከቤተመንግሥት እንዲወጡ ተደረገ

ታትሟል

የፕሬዝዳነት ጆ ባይደን ውሾች ከቤተመንግሥቱ ሠራተኞች ጋር መላመድ ባለመቻላቸው የተነሳ ወደ ቤታቸው እንዲሄዱ ተደርጓል።

ፕሬዝዳነት ጆ ባይደን ከመጠለያ አምጥተው ያሳደጉት እና 'ሜጀር' በማለት የሚጠሩት ውሻቸው አንድ የደኅንነት ሠራተኛ በመንከሱ ምክንያት ከቤተመንግሥት እንዲወጡ ተደርገዋል።

እንደ አሜሪካ የመገናኛ ብዙሃን ዘገባ ከሆነ ውሾቹ ዊልሚንግተን ዴላዌር ወደሚገኘው የባይደን ቤተሰቦች ቤት ተወስደዋል።

ውሾቹ የዋይት ሐውስ ሠራተኞች ላይ ጠባያቸው መቀያየሩ ተገልጿል።

ፕሬዝዳንት ባይደን ሜጀር የተሰኘው ውሻቸውን በ2018 ከማቆያ በመውሰድ ነው ያሳደጉት።

ሌላኛው ውሻ 'ቻምፕ' ደግሞ 13 ዓመቱ ነው ተብሏል።

ስሙ እንዳይጠቀስ የፈለገ አንድ ግለሰብ ለሲኤንኤን እንደገለፀው ሜጀር ሰዎች ሲያይ ይጮሃል፣ ይዘላል፣ ለመናከስም ይሞክራል።

ሁለቱም ውሾች ወደ ዋይት ሐውስ የመጡት ጆ ባይደን 46ኛው የአሜሪካ ፕሬዝዳንት በመሆን ቃለ መሃላ በፈፀሙ በአራተኛው ቀን ነበር።

የጆ ባይደን ባለቤት ጂል ባለፈው ወር ኬሊ ክላርክሰን ሾው ላይ ቀርባ ተቀዳሚ ተግባሯ ውሾቹ እንዲረጋጉ ማድረግ መሆኑን ገልጻ ነበር።

"አሳንስር ተጠቅመው ስለማያውቁ መጠቀም መልመድ አለባቸው። በርካታ ሰው እየተመለከታቸው መውጣት መልመድ አለባቸው፤ እንዲረጋጉ እና እንዲለምዱ ማድረግም ያስፈልጋል" ብላ ነበር።

አሜሪካውያን የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ እንዲያደርጉ በሚያሰሳስብ የቴሌቪዥን ማስታወቂያ ላይ ውሾቹ ከቀዳማይት እመቤት ጋር በመሆን ታይተዋል።

በተጨማሪም በታኅሣስ ወር የገና በዓልን አስመልክቶ በነበረ የመልካም ምኞት መግለጫ ሥነ ሥርዓት ላይም ታይተዋል።

ፕሬዝዳንቶች ወደ ዋይት ሐውስ ውሾቻቸውን ይዘው መግባት የተለመደ ሲሆን፤ ዶናልድ ትራምፕ ብቻ በ100 ዓመት ታሪክ ውስጥ ያለ ቤት እንስሳ በነጩ ቤተመንግሥት የኖሩ ፕሬዝዳንት ሆነው ተመዝግበዋል።