ፖፕ ፍራንሲስ በኢራቅ ከከፍተኛ የሺአ እስልምና መሪዎች ጋር ተነጋገሩ

ፖፕ ፍራንሲስ

የፎቶው ባለመብት, EPA

ታትሟል

ፖፕ ፍራንሲስ ታሪካዊ ነው በተባለው የኢራቅ ጉዟቸው ዛሬ ሁለተኛ ቀን ሆኗቸዋል። በሁለተኛ ቀን ጉብኝታቸውም የሺአ እስልምና ከፍተኛ መሪዎች ጋር እየተወያዩ እንደሆነ ተገልጿል።

ፖፕ ፍራንሲስ የሚሊየኖች የሺአ እስልምና ተከታዮች ሐይማኖታዊ መሪ ከሆኑት ታላቁ አያቶላህ አሊ አል ሲስታኒ ጋር እያደረጉት ያለው ውይይት በቅድስቲቷ ከተማ ናጃፍ እየተካሄደ ነው።

ፖፕ ፍራንሲስ ፍራንሲስ በኢራቅ የሚያደርጉት ጉብኝት ከኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ መከሰት በኋላ የመጀመሪያው ዓለም አቀፍ ጉዟቸው ነው።

ለአራት ቀናት የሚቆየው ይህ የጳጳሱ ጉብኝት በኢራቅ እየቀነሰ የመጣውን የክርስቲያኑን ሕብረተሰብ ለማነቃቃት ብሎም በተለያዩ ሐይማኖቶች መካከል የሚደረጉ ውይይቶችን ለማበረታታት ያለመ ነው።

የ84 ዓመቱ የካቶሊክ እምነት መሪ ፖፕ ፍራንሲስ የ90 ዓመቱ የሺአ መሪ ጋር የተለያዩ ሀይማኖቶች በጋራ መኖር ስለሚችሉባቸው ሁኔታዎችና በኢራቅ የክርስትያኖችን ሕይወት ማሻሻል በሚቻሉባቸው ሁኔታዎች ዙሪያ እንደሚነጋገሩ ይጠበቃል።

ፖፕ ፍራንሲስ ወደ ጥንታዊቷ ከተማ ኡር ጉዞ እንደሚኣደርጉም ተገልጿል። ይህች ከተማ በእስልምና፣ ከክርስትና እና በአይሁድ እምነት ትልቅ ቦታ የሚሰጠው ነብዩ አብራሃም እንደተወለደባት ይታመናል።

ወደ 10ሺህ የሚጠጉ የኢራቅ ጸጥታ አስከባሪ ኃይሎች የፖፕ ፍራንሲስ ደኅንነትን ለማረጋገጥ የሚሰማሩ ሲሆን በጳጳሱ ጉብኝት ወቅትም የወረርሽኙን ስርጭት ለመቆጣጠር ሰዓት እላፊ ታውጇል።

የሺአ ታጣቂ ቡድኖች የፖፕ ፍራንሲስን ጉብኝት በመቃወም 'በኢራቅ ጉዳይ ላይ የምዕራባውያን ተጽህኖን የሚያሳይ ነው' ብለውታል።

ፖፕ ፍራንሲስ አርብ ዕለት ልክ ባግዳድ አየር ማረፊያ ሲደርሱ ጠቅላይ ሚኒስትር ሙስጣፋ አል ካዲሚ የተቀበሏቸው ሲሆን ባደረጉት ንግግርም በኢራቅ ያለው ''አክራሪነትና ጸብ እንዲሁም መከፋፈልና አለመቻቻል'' መቆም አለባቸው ብለዋል።

'' ኢራቅ የጦርነትን አስከፊ ገጽታ በደንብ አይታዋለች። ሽብርና የሐይማኖት መከፋፈል ብዙ ዋጋ አስከፍሏል''

''በኢራቅ እየቀነሰ የመጣው የክርስትና እምነት ተከታዮች ቁጥር አሳሳቢ ነው። አነዚህ ዜጎች እንደማንናውም ኢራቃዊ መብት፣ ነጻነትና ግዴታ ሊሰጣቸው ይገባል'' ብለዋል።

በክርስትና እምነት የመጀመሪያ እምነቱ ተከታዮች ይኖሩበታል ተብሎ የሚታመነው ይህ አካባቢ ቀድሞ ከነበረው 1.4 ሚሊዮን ተከታዮች ቀንሶ በአሁኑ ሰአት የክርስቲያኖች ቁጥር 250 ሺ ብቻ ሆኗል።

ይህ ደግሞ ከአጠቃላይ የኢራቅ ህዝብ አንድ በመቶ ብቻ ነው።

ሳዳም ሁሴንን ያስወገደው የአሜሪካ ወረራን ተከተሎም በኢራቅ የክርስቲያን ማኅበረሰቡ ላይ ያተኮሩ ጥቃቶችን በመበራከታቸው ብዙዎች አገራቸውን ጥለው ተሰደዋል።

በአስር ሺዎች የሚቆጠሩትም አይሲስ እኤአ በ2014 የኢራቅን ሰሜናዊ ክፍል መቆጣጠሩን ተከትሎ ከኢራቅ ተሰደዋል።

አይሲስ ታሪካዊ አብያተ ክርስቲያናትን በማፍረስ፣ ንብረታቸውን በመውረስ፣ ግብር እዲከፍሉ በማድረግ፣ ሐይማኖታቸውን እንዲቀይሩ ማድረግ፣ እንዲሰደዱ ወይም ከሞት ጋር እንዲጋፈጡ ሲያደርግ ቆይቷል።

ምንም እንኳን ፖፕ ፍራንሲስ ኮሮረናቫይረስን ተከትሎ ብዙም እንቅስቃሴ እንደማያደርጉ ቢጠበቅም አንድም ይሁን ሁለት ቦታዎች ላይ ግን በርካቶች ሊሰበሰቡ እንደሚችሉ ይገመታል። በዚህም የቫይረሱን ስርጭት እንዳያባብሰው ተሰግቷል።