ጆን ገደርት፡ የቀድሞ የአሜሪካ ኦሊምፒክ አሰልጣኝ ሞተው ተገኙ

የፎቶው ባለመብት, Reuters
የቀድሞው የአሜሪካ ኦሊምፒክ የጂምናስቲክ አሰልጣኝ ሕይወታቸው አልፎ መገኘቱን ባለሥልጣናት አስታወቁ።
የቀድሞ አሰልጣኙ በወሲባዊ ጥቃትና በሕገ ወጥ የሰዎች ዝውውር ክስ ከቀረበባቸው ከሰዓታት በኋላ ራሳቸውን ማጥፋታቸውን ነው ባለሥልጣናቱ የገለፁት።
የሚቺጋን አቃቤ ሕግ ጆን ገደርት 24 ክስ ከቀረበባቸው ከሰዓታት በኋላ መሞታቸውን አረጋግጠዋል።
የቀድሞ አሰልጣኙ በታዳጊ ሴቶች ላይ ጭምር ቃላዊ፣ አካላዊ እና ወሲባዊ ጥቃት ፈፅመዋል የሚል ክስ ቀርቦባቸው ነበር።
ጆን እአአ በ2012 በነበረው የሴቶች ጂምናስቲክ ቡድን መሪ የነበሩ ሲሆን፤ ከዶክተር ላሪይ ናሳር ቡድን ጋር በቅርበት ይሰሩ ነበር።
ናሳር እአአ በ2018 ሥልጣናቸውን በመጠቀም ከ250 በላይ ሴቶች ላይ ጥቃት በማድረስ 300 የሚሆኑ ዓመታትን በእስር እንዲያሳልፉ ተበይኖባቸዋል።
በርካታ የጂምናስቲክ ስፖርተኞችም በናሳር የፍርድ ሂደት ምስክርነታቸውን ሲሰጡም ባላቸው አጸያፊ ጠባይ ክስ አቅርበውባቸዋል።
ገደርት እአአ በ2016 በናሳር ላይ ምርመራ በሚካሄድበት ጊዜ ለመርማሪዎች የሀሰት ቃል ሰጥተዋል የሚል ክስም ቀርቦባቸው ነበር።
ይህ በስፋት በሴቶች ላይ የተፈፀመው ጥቃት መጋለጡም፤ የአሜሪካ ጂምናስቲክ ላይ ጥብቅ ምርመራዎች እንዲካሄዱ ምክንያት ሆኗል።
ተቋሙ ለስፖርተኞች በሚያደርገው ጥበቃም ትችት ተሰንዝሮበታል።
የ63 ዓመቱ ገደርት፤ በሚቺጋን ናሳር የጂምናስቲክ ዶክተር ሆኖ ይሰራበት የነበረ የስልጠና ተቋም ነበራቸው።
ታዲያ ማክሰኞ ዕለት ከሰዓት ፍርድቤት እንደሚቀርቡ ተጠብቀው የነበረ ቢሆንም፤ እርሳቸው ግን አልተገኙም ብሏል- የጠቅላይ አቃቤ ሕግ ጽ/ቤት።
የሚቺጋን ጠቅላይ አቃቤ ሕግ ዳና ኔሴል በሰጡት መግለጫ "ጆን ገደርት ራሱን ካጠፋ በኋላ አስክሬኑ መገኘቱ ለቢሮየ ማሳወቂያ ደርሷል" ብለዋል።
" ይህ በዚህ ሂደት ለተሳተፉት ሁሉ የአሳዛኝ ታሪክ አሳዛኝ መጨረሻ ነው" ሲሉም ጠቅላይ አቃቤ ሕጉ ተናግረዋል።














