በጣሊያን የመሬት መንሸራተት በርካታ የሬሳ ሳጥኖችን ወደ ባሕር ከተተ

የመሬት መንሸራተት የገጠመው አካባቢ

የፎቶው ባለመብት, Vigili del Fuoco

የምስሉ መግለጫ, የመሬት መንሸራተት የገጠመው አካባቢ
ታትሟል

ሰኞ ዕለት በሰሜን ምዕራብ ጣሊያን የደረሰ የመሬት መንሸራት በመቶዎች የሚቆጠሩ የሬሳ ሳጥኖችን ካረፉበት የቀብር ስፍራ ወደ ባሕር ከቷቸዋል።

በመሬት መንሸራተቱ ሳቢያ ካረፉበት መካነ መቃብር ወደ ባሕሩ የገቡትን የሬሣ ሳጥኖችን 200 ገደማ የሚሆኑ የአደጋ ጊዜ ሠራተኞች ጄኖዋ አካባቢ ሲያፈላልጉ አንድ ተንቀሳቀሽ ምስል አሳይቷል።

ከመቃብሩ በታች የነበሩ ሁለት ቤተ-ክርስትያናትም ተጠርገው ወደ ባሕር ሰጥመዋል።

የአካካቢው ከንቲባ የባሕር ጠረፍ ላይ ለምትገኘው ኮረብታማ ከተማ ይህ "መጥፎ ዜና" ነው ሲሉ ለመገናኛ ብዙሃን ተናግረዋል።

መቃብሩ በባሕላዊ የጣልያን ቤት አሠራር የተገነባ ነበር።

በአካባቢው የነበሩ ሠራተኞች የመሬት መንሸራተቱ ቤቶችን እየቦዳደሰ ሲወስድ የሚያሳይ ምስል በስልካቸው አስቀርተዋል።

የመሬት መንሸራተቱ ከጥቂት ሰከንዶች በኋላ አፋፍ ላይ ያሉ ቤቶች እየቆረሰ ወደ ሊጓሪያን ባሕር አስጥሟል።

በርካታ የሬሳ ሳጥኖች ጭቃማ በሆነው የባሕር ዳርቻ ላይ ተንሳፈው የሚያሳዩ ፎቶዎችም ተሠራጭተዋል።

"ልክ ዛሬ የተከሰተውን ዓይነት አደጋ መገመትም ሆነ መከላከል እጅግ አዳጋች ነው" ብለዋል የከተማዋ ከንቲባ ፍራንቼስኮ ኦሊቫሪ።

የአካባቢው ባለሥልጣናት እንዳሉት በአካባቢው የሚሠሩ ሰዎች ከቀናት በፊት የተሰነጠቀ ግድግዳ አይተው አደጋ ሊኖር እንደሚችል አስጠንቅቀው ነበር።

ከዚህ ማስጠንቀቂያ በኋላ ነዋሪዎች ከአካባቢው እንዲሸሹ መደረጉም ተሰምቷል።

የእሳት አደጋ ሠራተኞችና የባሕር ዳርቻ ጠባቂዎች የአደጋ ጊዜ ሠራተኞችን ሲተባበሩ ታይተዋል።

ከሰጠሙት 200 ገደማ የአስከሬን ሳጥኖች መካከል 10 ያህሉን ከባሕር ማውጣት የተቻለ ሲሆን ባለሥልጣናቱ አካባቢውን አጥረው ሳጥኖቹ ወደ ባሕሩ መሃል እንዳይገባ እያደረጉ ነው ተብሏል።