እስረኞች እንዲገደሉ አድርጓል የተባለው ሶሪያዊ ጀርመን ውስጥ ተፈረደበት

የኢያድ አል ጋሪብ ችሎት የተጀመረው ባለፈው ዓመት

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የምስሉ መግለጫ, የኢያድ አል ጋሪብ ችሎት የተጀመረው ባለፈው ዓመት
ታትሟል

ጀርመን ያለ አንድ ፍርድ ቤት የቀድሞውን የሶሪያ የደኅንነት ክፍል ሠራተኛ በሰብዓዊ ፍጡር ላይ በፈፀመው ወንጀል በአራት ዓመት ተኩል እስር እንዲቀጣ በይኖበታል።

የኮብሌንዝ ዐቃቤ ሕግ ኢያድ አል-ጋሪብ በፈረንጆቹ 2011 በነበረው ተቃውሞ ላይ የተሳተፉ ሰዎች እንዲታሠሩ እንዲሁም ተሰቃይተው ለመሞታቸው ምክንያት ነው ሲል ተከራክሯል።

በሶሪያው ፕሬዝደንት ባሽር አል-አሳድ አገዛዝ ዘመን ተፈፅመዋል በተባሉ ወንጀሎች ዙሪያ ፍርድ ሲሰጥ ይህ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው።

ሌላኛው የ58 ዓመቱ ሶሪያዊ አንዋር ራስላን አሁንም የፍርድ ሂደቱ እየታየ ይገኛል።

ሁለቱም ግለሰቦች በሶሪያ ያለውን የእርስ በርስ ግጭት ሸሽተው ወደ ጀመርን በመሰደድ ጥገኝነት ጠይቀዋል። ነገር ግን በፈረንጆቹ 2019 በቁጥጥር ሥር ውለዋል።

የጀመርን ዐቃቤ ሕግጋት ሰዎችን በቁጥጥር ሥር ያዋሏቸው ከባድ ወንጀል የፈፀሙ ሰዎች "በዓለም አቀፍ ሕግ ይዳኙ" የሚለውን አንቀፅ አስታከው ነው።

የሁለቱ ተከሳሾች ጠበቆች ሰዎች ድርጊቱን የፈፀሙት ስለታዘዙና ባያደርጉት የሚመጣውን መዘዝ በመፍራት ነው ሲሉ ተከራክረዋል።

በፈረንጆቹ 2011 በሶሪያው መሪ ባሽር አል-አሳድ ላይ የተነሳውን ተቃውሞ በመቅጨት ረገድ የደኅንነት መሥሪያ ቤቱ ጉልህ ሚና ተጫውቷል።

ለአንዳንድ ሶሪያዊያን የሁለቱ ሰዎች መታሠርና ለፍርድ መቅረብ ምናልባትን ሌሎች በርካታ ወንጀሎች ለፍርድ ይቀርባሉ የሚል ተስፋን የሰጠ ነው።

ሰዎቹ ላይ የቀረበው ክስ ምንድነው?

ዐቃቤ ሕግ ሁለቱ ሰዎች የገዥው መንግሥት መሣሪያ በመሆን ዜጎችን አሰቃይተዋል ሲሉ ተከራክረዋል።

ኢያድ አል-ጋሪብ፤ ለጄኔራል ኢንተለጀንስ ዳይሬክቶሬት በሚሠራበት ወቅት ቢያንስ 30 ተቃዋሚዎችን ደማስቆ ያለ አደገኛ እስር ቤት እንዲገቡና እንዲሰቃዩ አድርጓል ተብሎ ተከሷል።

ኢያድ አል-ጋሪብ ተቃዋሚዎችን ለማገዝ ከአሳድ አገዛዝ ራሱን ማግለሉንና በ2013 ከሶሪያ ተሰዶ በ2018 ጀርመን መግባቱን ለፍርድ ቤቱ ተናግሯል።

አንዋር ራስላን ደግሞ ከ2011 እስከ 12 ባለው ጊዜ ቢያንስ 4 ሺህ ሰዎች ሲሰቃዩ እጁ አለበት ተብሎ ነው የተከሰሰው።

በተጨማሪ በ58 ሰዎች ግድያ እንዲሁም በመድፈርና በፆታዊ ጥቃት ተከሷል።

ሰውዬው በደኅንነት መስሪያ ቤቱ የሚመራው የደማስቆው አል-ካቲብ እስር ቤት ከፍተኛ ባለሥልጣን ነበር ተብሏል።

እስር ቤቱ "ምድረ-ገነት" የሚል ቅፅል ስያሜ አለው።

ግለሰቡ ጥፋተኛ ሆኖ ከተገኘ እስከ ዕድሜ ልክ እስራት ድረስ ይጠብቀዋል ተብሏል።

ለበርካታ ሰዓታት የዘለቀ ምስክርነት በሰዎቹ ላይ እንዲሰጥ ተድርጓል። ምስክርነት የሰጡ ሰዎች ወደ እስር ቤቱ ሲመጡ ደረሰብን ያሉን ግፍ ለፍርድ ቤቱ ተናግረዋል።

አብዛኛዎቹ ምስክሮች ክፉኛ እንደተደበደቡ፣ እንደተደፈሩና ለሰዓታት ጣሪያ ላይ ተሰቅለው እንደተሰቃዩ ለችሎቱ ተናግረዋል።

ቄሳር በተሰኘና ከወታደራዊ ኃይል አምልጦ በወጣ ግለሰብ እጅ ያሉ በርካታ ፎቶዎችም እንደማስረጃ ቀርበዋል።

የአሳድ መንግሥት በተደጋጋሚ የቀረበበትን ክስ አልፈፀምኩም ሲል አስተባብሏል።

ከሁለቱ ግለሰቦች በተጨማሪ ሌሎች የሶሪያ የቀድሞ ባለሥልጣናት ጀርመን ውስጥ ወንጀላቸው እየተመረመረ ይገኛል።

በ2011 የሶሪያውን ፕሬዝደንት በመቃወም በርካቶች ወደ አደባባይ መውጣታቸው ይታወሳል።

የአል-አሳድ መንግሥት ለዚህ ተቃውሞ ምላሽ የሰጠው ኃይል በታከለበት መንገድ ነበር።

በአሳድ ወታደሮችን አገዛዙን በሚቃወሙ ታጣቂዎች መካከል ነገሮች ከረው አሁን አገሪቱ የእርስ በርስ ጦርነት ውስጥ ትገኛለች።

አስር ዓመት በደፈነው የአገሪቱ ነውጥ ቢያንስ 387 ሺህ ሰዎች እንደተገደሉ መቀመጫውን እንግሊዝ ያደረገ አንድ ድርጅት ይጠቁማል።

ድርጅቱ ከዚህ ቁጥር በተጨማሪ በመንግሥት እስር ቤቶች የተገደሉ 88 ሺህ ገደማ ሰዎች አሉ ይላል።

አሁን የአሳድ ወታደሮች ዋና ዋና ከተሞችን ተቆጣጥረው ሲገኙ ታጣቂዎቹ ደግሞ ከከተሞች ውጪ ይገኛሉ።