ኮሮናቫይረስ፡ የትኞቹ የአፍሪካ ሃገራት ክትባት ጀመሩ? ሌሎቹስ መች ይጀምራሉ?

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በአህጉረ አፍሪካ ቢያንስ 100 ሺህ ያክል ሰዎች እስካሁን በኮሮናቫይረስ ምክንያት ሕይወታቸውን አጥተዋል። አህጉሪቱ የኮሮናቫይረስ ክትባትን በተገቢው መንገድ እየሰጠች አይደለም እየተባለች ትታማለች።
ለመሆኑ የትኞቹ የአህጉሪቱ ሃገራት ናች ክትባት መስጠት የጀመሩት?
የዓለም ሃገራት የኮቪድ-19 ክትባት ለማግኘት ፉክክር ላይ ናቸው። የአፍሪካ ሃገራት ግን ሃብታም ከሚባሉት ሃገራት ጋር ሲነፃፀር ወደኋላ የቀሩ ይመስላሉ።
"በጣም ተጋላጭ የሆኑ የአፍሪካ ሃገራት ክትባት የማግኘት ተራቸው እስኪደርስ ድረስ እየጠቁ ነገር ግን እምብዛም ተጋላጭ ያልሆኑ ሃብታም ሃገራት ክትባቱን ሲያገኙ ማየት ፍትሃዊ አይደለም" ይላሉ በዓለም ጤና ድርጅት የአፍሪካ ዳይሬክተር ማትሺዲሶ ሞዬቲ።
የፈረንሳዩ ፕሬዝደንት ኢማኑኤል ማኽሮ የአውሮፓና ሃገራትና አሜሪካ ከክትባቶቻቸው ቀንሰው ለአፍሪካ ሃገራት መስጠት አለባቸው ሲሉ ምክረ ሐሳብ አመንጭተው ነበር።
የተወሰኑ ክትባቶች ለአፍሪካ ሃገራት በፍጥነት ሊዳረሱ ይገባል ይላሉ ፕሬዝደንቱ።
አፍሪካ ውስጥ እስካሁን ድረስ ክትባት ማግኘት የቻሉት ከፋብሪካዎች በቀጥታ መግዛት የቻሉና ከሩስያ፣ ቻይና፣ ሕንድና ዩናይትድ አራብ ኤሜሬትስ በእርዳታ መልክ ያገኙ ሃገራት ናቸው።
የአፍሪካ ሃገራት በዓለም አቀፍና ቀጣናዊ ፕሮግራሞች ክትባት ለማግኘት ተስፋ አድርገዋል።
አንደኛው ፕሮግራም ኮቫክስ የተሰኘው ነው። ይህ ፕሮግራም ሁሉም ሃገራት ክትባት ያገኙ ዘንድ ያለመ ነው።
የዓለም ጤና ድርጅት ከያዝነው የፈረንጆች ወር መጨረሻ ጀምሮ የአፍሪካ ሃገራት ክትባት ማግኘት ይጀምራሉ ብሎ ይገምታል።
በዚህ ወቅት የሚሠራጩ 90 ሚሊዮን ክትባቶች የአህጉሪቱን 3 በመቶ ሕዝብ ይከትባሉ ተብሎ ይጠበቃል።
ይህ ክትባት በጣም ተጋላጭ ለሆኑና በቫይረሱ ምክንያት የበለጠ አደጋ ለሚደርስባቸው እንደ ጤና ባለሙያዎች ላሉ የሕብረተሰብ አካላት የሚከፋፈል ነው።
የኮቫክስ ዓላማ 600 ሚሊዮን ክትባት ማግኘት ነው። ይህ የክትባት መጠን በፈረንጆቹ 2021 መጨረሻ ባለው የአህጉሪቱን 20 በመቶ ሰው ይከትባል።
የአፍሪካ በሽታ ቁጥጥርና መከላከል ማዕከል ኃላፊ ጆን ንኬንጋሶንግ ግን ይህ የክትባት መጠን በሽታውን ከአፍሪካ ነቅሎ ለማስወጣት በቂ ነው ብለው አያምኑም።
እሳቸው እንደሚሉት የአፍሪካ ሃገራት ቢያንስ 60 በመቶ የሚሆነውን ሕዝባቸውን መከተብ አለባቸው።
የአፍሪካ ሕብረትም በሃምሳ አምስቱ የአፍሪካ ሃገራት ስም ክትባት ለማግኘት ደፋ ቀና እያለ ነው።
የአፍሪካ ሞባይል ኔትወርክ አቅራቢ ድርጅት የሆነው ኤምቲኤን 25 ሚሊዮን ዶላር በማዋጣት ለአፍሪካ የጤና ባለሙያዎች የሚሆን ሰባት ሚሊዮን ክትባት ለማግኘት እየጣረ ነው።
የበሽታ ቁጥጥር ማዕከሉ እንደሚለው በኤምቲኤን በኩል የተገኘ አንድ ሚሊዮን ክትባት ለ20 ሃገራት በያዝነው ወር መጨረሻ ይከፋፈላል።
የትኞቹ ሃገራት ቀድመው ክትባቱን እንደሚያገኙ ግን የተባለ ነገር የለም።
ዜጎቻቸውን መከተብ የቻሉ ሃገራት የትኞቹ ናቸው?
ምንም እንኳ ጥቂት ሃገራት ባለፈው ወር ክትባት መስጠት ቢጀምሩም አብዛኛዎቹ ሃገራት ግን ገና አልጀመሩም።
በሰሜን አፍሪካ ክትባት መስጠት የጀመሩት ሃገራት ሞሮኮ፣ አልጄሪያና ግብፅ ናቸው። ከሰሃራ በታች ባሉ አፍሪካ አገራት ደግሞ ደቡብ አፍሪካ፣ ሲሼልስ፣ ሩዋንዳ፣ ሞሪሺዬስና ዚምባቡዌ ይገኛሉ።
እንደ ኢኳቶሪያል ጊኒና ሴኔጋል ያሉ ሃገራት የመጀመሪያውን ዙር የሳይኖፋርም ክትባት ተቀብለዋል፤ መከተብ ግን አልጀመሩም።
በአህጉሪቱ በወረርሽኙ ክፉኛ የተጠቃችው ደቡብ አፍሪካ አስትራዜኔካ የተሰኘውን ክትባት ለመከተብ ዕቅድ ይዛ ነበር። ነገር ግን ክትባቱ በአዲሱ የኮሮናቫይረስ ዝርያ ላይ ያለው ኃያልነት አናሳ ነበው በሚል ሰርዛዋለች።
ነገር ግን አሁን ጆንሰን ኤንድ ጆንሰን ከተሰኘው ፋብሪካ የተገኘው ክትባት ለአዲሱ ዝርያ ፍቱን ነው በሚል መከተብ ጀምራለች።
ደቡብ አፍሪካ ከሕንዱ አቅራቢ ያገኘችውን አድን ሚሊዮን የአስትራዜኔካ ክትባት ሌሎች የአፍሪካ ሃገራት መጠቀም ከፈለጉ በሚል ለአፍሪካ ሕብረት ሰጥታለች።












