"ከሞት ይልቅ የምፈራው መኖርን ነው"

አሌክዞ ፓዝ

የፎቶው ባለመብት, Nanouk Films

የምስሉ መግለጫ, አሌክዞ ፓዝ
ታትሟል

በ20ዎቹ መጀመሪያ ላይ የሚገኝ ወጣት ለመኖር ሲጓጓ እንጂ ሕይወትን ሲፈራ ማየት የተለመደ አይደለም።

ስፔናዊው አሌክዞ ፓዝ ግን ሞትን ይመርጣል፤ ሕይወትን ይፈራል። በሕይወት መቆየቱን ሲያስብ ይንዘፈዘፋል፤ በፍርሃት ላብ ያሰምጠዋል።

አሌክዞ 8 ዓመቱ ላይ መጥፎ እጣ ገጠመው። 90 በመቶ ሰውነቱ በእሳት ተለበለበ። ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ይኸው በስቃይ ውስጥ ለመኖር ተገዷል። ከሞት ይልቅ መኖርን ቢፈራ እንዴት ይፈረድበታል?

አሌክሶ ፓዝ ለቢቢሲ ሲናገር፣ "በእያንዳንዱ ቀን ከአልጋዬ እንድነቃና እንድኖር የሚያደርገኝ ብቸኛው ነገር ቁጣ ነው" ይላል።

"ቁጣ በሕይወት እንድቆይ አድርጎኛል። ቁስሌ እየጠገግልኝ ያለውም ለዚያ ይመስለኛል" ይላል።

የራሱን ታሪክ እንዲህ ይተርካል።

"እያዳንዷ ትንፋሽ ለኔ ስቃይ ት"

ከአባቴ ጋር ነዳጅ የጫነ ቦቴ ውስጥ ነበርን። በአውራ ጎዳና ላይ ቦቴው ከባድ የመኪና አደጋ ደረሰበት። እንቅልፍ እያንገላታኝ ነበር። ስነቃ ሰውነቴ እንደ ጭድ ይነዳል። ከዚህ በኋላ የሆነውን አላውቅም።

ተአምር ገደብ የለውምና ተረፍኩ። ምን አለበት ባልተረፍኩ? ምናለ ሞቼ በሆነ።

ያልተኖረ ልጅነቴን፣ ያልተኖረውን ጉርምስናዬን በሆስፒታል ኖርኩት። ምን አማራጭ አለኝ?

ዕድሜ ዘመኔን ቀዶ ጥገና አደርጋለሁ። ዕድሜ ልኬን ከስቃይ ጋር እኖራለሁ። ቅዠት እና ቁጣ፣ ቁስልና ነበልባል ይቀባበሉኛል።

ሰዎች የሚሰበሰቡባቸውን ሥፍራዎች እንደ ጦር ነው የምፈራው። ሰዎች ሲያፈጡብኝ ቁስሌ የመረቀዘ ያህል ይሰማኛል። የሰው ዓይን መርፌ ሆኖብኛል።

ደግሞ ተጠራጣሪ ነኝ። ሰዎች ከንፈር ሲመጡልኝ ራሱ ህመም እንጂ ሰላም አይሰማኝም።

አሌክዞ ፓዝ

የፎቶው ባለመብት, Nanouk Films

በቅርቡ ግን ታሪኬን በዘጋቢ ፊልም ለሕዝብ እንዲደርስ ፈቅጃለሁ። ዘ ፋየር ኪድ (The Fire Kid-El Niño de Fuego) ይሰኛል ዘጋቢ ፊልሙ።

እውነት ለመናገር ካሜራ ለዓመታት ተደቅኖብኝ ስቃዬን ሲመዘግብ ምቾት ሊሰማኝ አይችልም።

ነገር ግን አስቀድሜ ተናግሪያለሁ። ዘጋቢ ፊልሙ ሲጀምር ተመልካቾች ከእኔ ምንም መልካም ነገር እንዳይጠብቁ አስጠንቅቂያለሁ። አንዳች የሚያነቃቃ፣ አንዳች ብርታት የሚሰጥ ንግግር በፍጹም እንዳይጠብቁ አደራ ብያለሁ።

ጥሬ የስቃይ ሕይወቴን ማየት ከፈቀዱ ብቻ ነው የእኔን ዘጋቢ ፊልም ሰዎች ማየት ያለባቸው እላለሁ።

በሕይወቴ ምንንም ነገር ታግዬ አላሸንፍኩም እኮ፤ ድል ያደረኩ ጀግና አይደለሁም፤ የስቃይ ተምሳሌት ነኝ። የእኔ ብቸኛ ጥንካሬ ከሞት ይልቅ ሕይወትን መፍራቴ ነው፤ ይህ ጥንካሬ ከተባለ ማለቴ ነው።

ሰዎች እኔ ብርቱ ሰው እንደሆንኩ ይነግሩኛል። ምኑ ነው ብርቱ ያስባለኝ ስላቸው 90 ከመቶ ሰውነትህ ተቃጥሎ ሕይወት መኖርን ቀጥለሃል ይሉኛል።

አያውቁም ሞት ምርጫዬ እንደሆነ፤ አያውቁም ሕይወት ሞት እንደሆነብኝ።

ሰውነቴ በእሳት ሲነድ የነበረው ቅጽበት ከአእምሮዬ አልጠፋም። አሁንም እንዳለ ነው። ልረሳው አልቻልኩም፤ ከትዝታ ማኅደሬ አልፋቅ አለኝ። ምናባቴ ላድርግ!?

ይህ የአደጋ ክስተት ቀንና ሌሊት ያባንነኛል። እያስጮኸ ያነቃኛል፤ ያስቃዠኛል። ሰላማዊ እንቅልፍ የማገኝባቸው ቅጽበቶች ጥቂት ናቸው።

አንዳንድ ቀናት ከእንቅልፌ የምነቃው በእሳት ስለበለብ እየታየኝ፣ በላብ ተዘፍቄ እየጮህኩ ነው። ብዙ ሰዎች ቆዳዬ መለብለቡን ነው የሚመለከቱት። ከቆዳዬ ሥር ያለውን የስሜት ህመም የሚያይልኝ ማንም የለም።

ከነዳጅ ጋር ነው አብሬ የነደድኩት። ያ አደጋ እኔነቴን መሉ በሙሉ ነው የቆየረው። ራሴ የለሁም። እኔን እሳት በልቶኛል። አሌክዞ ፓዝ የለም። አሁን ያለው የእኔ ቅሪት ነው። የአሌክዞ ፓዝ ቅሪት።

አሌክዞ ፓዝ ከፊልም ዳይሬክትር ኢግናሲዮ አኮንሺያ

የፎቶው ባለመብት, Nanouk Films

የምስሉ መግለጫ, አሌክዞ ፓዝ ከፊልም ዳይሬክትር ኢግናሲዮ አኮንሺያ

አንዳንድ ጊዜ የልጅነት ፎቶዬን ሳየው ራሴን ማወቅ ይሳነኛል። እያወራሁ ያለሁት ስለ መልክ አይደለም። እያወራሁ ያለሁት ስለ ስሜት ነው፤ ስለ ተስፋ ማጣት። ከዚህ ዓለም ስለመሰናበት ነው። መኖርን ስለመፍራት ነው።

ስሜ አሌክዞ ነው። አሌክዞ ግን አሁን የምታዩት እኔ አይደለሁም ብያችኋለሁ። አሌክዞ ስሜ ነው እንጂ እኔ አይደለሁም። እኔማ በልጅነቴ አለፍኩ። አሁን አጽሜ ነው ያለው አልኳችሁ።

ዘጋቢ ፊልሙ ከታየ በኋላ በርካታ ሰዎች የእኔ ታሪክ ለእነርሱ እንደረዳቸው ነግረውኛል። አልዋሻችሁም ያ የተወሰነ መልካም ስሜት እንዲሰማኝ ምክንያት ሆኗል።

መጀመሪያ የፊልሙ ርዕስ አላስደሰኝም ነበር። The Fire Kid የሚለው ርዕስ አልወደድኩትም። እኔና እሳትን ለምን ያጣምራል አልኩ። በኋላ ላይ ግን ቅጽል ስሜ ሆነ። አሁን ለመድኩት። ከስቃዩ አንጻር ለስሜ የምጨነቅበት ቅንጦት የለኝም።

ሰዎች ድንገት ሲያዩኝ ወደኔ ይጠጉና ሕይወቴን በአንተ ተለወጠ ብለው ያሞግሱኛል። መቼስ ወደደኩም ጠላሁ እንደዛ ሲሉኝ በእኔ ላይ ተጽእኖ ማሳደሩ አይቀርም።

ሰዎች እየመጡ ሲያመሰግኑኝ አንዳንድ ጊዜ ራሴን ማታለለል ሁሉ ይቃጣኛል። አይዞን ፓዝ አሁን ሕይወትህ እየተቀየረ ነው እለዋለሁ ራሴን።

ሌላው ተስፋዬ ሙዚቃ ነው።

ይገርመኛል።

ብዙ ሰዎች አይዞህ ሁሉም ነገር መልካም ይሆናል ይሉኛል። ውሸት ነው። ሁሉም ነገር መልካም አይሆንም። ቢያንስ ለእኔ እንደዛ ሆኖልኝ አያውቅም።

እንዲያውም ለእኔ እንዳንዱ ደቂቃ ህመም ነው። የሆድ ህመም፣ የጡንቻ ህመም፣ የአጥንት ህመም። ከስቃይ ወደ ስቃይ…፣ ከኡኡታ ወደ ኡኡታ። ጭንቀት ጥበት።

ምኑን ነው "ምንም አይደል" [It's OKAY] የሚሉኝ? ነው እንጂ! [It's not Okay!]

አሁን ትንሽ ህመም መለስ የሚልልኝ ሙዚቃ ስጫወት ነው። ትንሽ ተስፋ የሚፈነጥቅልኝ ያኔ ነው። ትንሽ ብርሃን በሙዚቃ ውስጥ ትታየኛለች።

የቀድሞ የቦክስ ሻምፒዮን፣ እስረኛና በኋላም ራፐር ኢሳክ ሪል (ቻካ) ተምሳሌቴ ነው።

እውነት መናገር አለብኝ። ሙዚቀኛ አይደለሁም። በሙዚቃ የትም እንደማልደርስ አውቃለሁ። እኔ ያበቃልኝ ሰው ነኝ። በሕይወት ማሳካት የምፈልገው ምንም ነገር የለም።

መኖርን ከሞተ በላይ ለሚፈራ ሰው ምን ተስፋ አለውና።

ሆኖም ግድግዳውን በብስጭት በቡጢ ከምነርተው ጥቂት የሙዚቃ ስንኞችን ጽፌ ሳዜም ህመሜ መለስ ይልልኛል። ቁጣዬም ለቅጽበትም ቢሆን ይበርድልኛል። ስቃዬ ግን ቀጣይ ነው። የማያባራ!