ለወራት ኮሮና ያልታዩባት ኒውዚላንድ ትልቋ ከተማዋ ላይ የእንቅስቃሴ ገደብ ጣለች

ታትሟል

የኒውዚላንድ ጠቅላይ ሚኒስትር ጃሲንዳ አርደን የአገሪቷ ትልቋ ከተማ፣ ኦክላንድ ሙሉ በሙሉ ውሸባ እንድትገባ ትእዛዝ አስተላልፈዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሯ ይህንን ውሳኔ ያስተላለፉት ሶስት አዲስ የኮሮናቫይረስ ህሙማን መገኘታቸውን ተከትሎ ነው።

ይህ እርምጃ ለሶስት ቀናት ያህል ይቆያል የተባለ ሲሆን ነዋሪዎችም በቤታቸው ተወስነው እንዲቀመጡ ተነግሯቸዋል።

አዳዲስ ህሙማን መገኘታቸውን ተከትሎ አገራቸው ጠበቅ ያለ እርምጃን እንደምትወስድ ጠቅላይ ሚኒስትሯ ተናግረዋል።

በአለማችን ካሉ አገራት መካከል የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝን ስርጭት በመግታት ከፍተኛ ውደሳ ያተረፈችው ኒውዚላንድ ለወራት ያህልም የማህበረሰብ ስርጭት አልተመዘገባባትም ነበር ተብሏል።

ገና ወረርሽኙ በተከሰተበት ወቅት ነው ዜጎች ላልሆኑ የአለማችን መንገደኞች ድንበሯን የዘጋችው። በዚህም የተዋጣ ስራ ሰርታለች ተብሏል።

አምስት ሚሊዮን የህዝብ ቁጥር ያላት ኒውዚላንድ 2 ሺህ 300 ሰዎች በቫይረሱ የተያዙበት ሲሆን ያጣቻቸውም ሰዎች ቁጥር 25 ነው።

በኦክላንድ ላይ በተጣለው የእንቅስቃሴ ገደብ መሰረት 1.7 ሚሊዮን የሚሆኑ የክልሉ ነዋሪዎች መሰረታዊ የሆኑ ሸቀጦችን ለመሸመትና ለስራ ካልሆነ በስተቀር በቤታቸው ተወስነው መቀመጥ አስገዳጅ ሆኗል።

ትምህርት ቤቶችና መሰረታዊ ሸቀጦችን ያልያዙ መደብሮችም ተዘግተው እንዲቆዩ ተወስኗል።

በነዚህ ሶስት ቀናት ውስጥ መንግሥት የበለጠ መረጃ እንዲያጠናክርና ከፍተኛ ቁጥር ያለው ምርመራ በማድረግ የማህበረሰብ ስርጭት አለ ወይ የሚለውን ለመወሰን የሚያስችል ነው ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትሯ።

ሌሎች ከተሞች እንዲሁ በተጠንቀቅ ላይ እንዲሆኑ ቢነገራቸውም ትምህርት ቤቶችም ሆኑ የንግድ ተቋማት ክፍት ናቸው።

ሆኖም ነዋሪዎች ወደ ስራ ቦታ አዘውትረው ከመሄድ ይልቅ አማራጭ መንገዶችን እንዲጠቀሙ መልዕክት ተላልፎላቸዋል።

በደቡባዊቷ ኦክላንድ ነዋሪ የሆኑ ባልና ሚስትና ልጃቸው በኮሮናቫይረስ እንደተያዙ የተነገረው በዛሬው ዕለት ነው።

የኒውዚላንድ የጤና ዳይሬክተር ጄኔራል ዶክተር አሽሊ ብሉምፊልድ እንዳሉት "አዲሱ የቫይረስ ዝርያ እንደሆነ በማሰብ እየሰራን ነው" ማለታቸውን ስታፍ ኦ ኤንዚ ዘግቧል።