ቻይና ለአለም ጤና ድርጅት ቁልፍ የተባለ መረጃ መከልከሏ ተገለፀ

ታትሟል

ቻይና የኮሮናቫይረስን አመጣጥ እየመረመረ ላለው የአለም አቀፉ ጤና ድርጅት ቡድን ቁልፍ የሆኑ መረጃ መከልከሏን የመርማሪው ቡድን አባል ተናግረዋል።

የስነህይወት ተመራማሪው ዶሚኒክ ድዋየር ቡድኑ መጀመሪያ ተመዘገቡ የተባሉ ህሙማንን ጥሬ መረጃ እንዲሰጧቸው መጠያቃቸውንና ይህም ደግሞ የተለመደ አሰራር መሆኑን ለሮይተርስ፣ ዋል ስትሪት ጆርናልና ኒውዮርክ ታይምስ ተናግረዋል።

ነገር ግን በጠየቁት መሰረት ሳይሆን ያገኙት አጭር ማጠቃለያ ነው።

መርማሪዎቹ በአውሮፓውያኑ ታህሳስ 2019 በኮሮናቫይረስ የተያዙ የመጀመሪያ ህሙማን የተባሉ 174 ኬዞችን ጥሬ መረጃ እንዲሰጣቸው መጠየቃቸውን ሮይተርስ ፕሮፌሰር ዶሚኒክን ዋቢ አድርጎ ዘግቧል።

መጀመሪያ ከተያዙ መካከል ቫይረሱ ተገኝቶበታል የተባለው የውሃን የስጋ ገበያ ጋር ንክኪ አላቸው የተባሉ ግማሾቹ የሚሆኑት ብቻ ናቸው።

"ለዚያም ነው ይህንን መረጃ እንዲሰጠን አጥብቀን እየጠየቅን ያለነው። ለምን መረጃውን አይሰጡንም? በዚህ ላይ ምንም ማለት አልችልም። ፖለቲካዊ ይሁን፤ አስቸጋሪ ስለሆነ ይሁን? ወይም መረጃው ሊኖርበት ያልቻለው ሌላ ምክንያት ይኖር ይሆን ወይ የሚለውን አላውቅም። ያው ማድረግ የሚቻለው የተለያዩ ግምቶችን ማስቀመጥ ነው" ብለዋል።

ቲያ ኮልሰን ፊሸር የተባሉ የመርማሪው ቡድን አባልና የወረርሽኝ ከፍተኛ ባለሙያ በበኩላቸው ምርመራው በከፍተኛ ሁኔታ "ጂኦ ፖለቲካል" መልክ እንዳለው ለኒውዮርክ ታይምስ ተናግረዋል።

"ቻይና ለምርመራው በሯን እንድትከፍት ምን ያህል ጫና እየተደረገባት እንደሆነ ሁላችንም የምናውቀው ነው። ከዚያም ጋር ተያይዞ ከፍተኛ ወቀሳዎች እየቀረቡ ነው" ብለዋል ተመራማሪዋ

በሚቀጥለው ሳምንት ይወጣል ተብሎ በሚጠበቀው የመርማሪው ቡድን የመጨረሻ ሪፖርት የመረጃዎች ክልከላ እንደሚካተት ፕሮፌሰር ዶሚኒክ ይናገራሉ።

ቻይና ለዚህ ክስ ምንም አይነት ምላሽ ባትሰጥም ከዚህ ቀደም ከአለም አቀፉ ጤና ድርጅት ጋር ለመተባበርና ግልፅ በሆነ መንገድ ለመስራት ፈቃደኛ ነኝ በማለት በተደጋጋሚ ተናግራለች።

ወረርሽኙ ከተከሰተባት ዕለት ጀምሮ አሜሪካ መረጃዎችን እንድትሰጥ ስትጎተጉት የነበረ ሲሆን በአለም አቀፉ ጤና ድርጅት ሪፖርት ላይ "ከፍተኛ ስጋት ተፈጥሮብኛል" ስትል ነበር።

ባለፈው ሳምንት የኮሮናቫይረስ በውሃን ከተማ ከሚገኝ ላቦራቶሪ አምልጦ የወጣ ነው የሚባለውን አወዛጋቢ ፅንሰ ሃሳብ ቡድኑ "ሊፈጠር የማይችል" ነገር ነው በማለት ማጣጣሉ ይታወሳል።

በአለማችን የመጀመሪያ የኮሮናቫይረስ ህሙማን የታዩት በአውሮፓውያኑ 2019 በውሃን ከተማ ነው።

በአሜሪካው የጆንስ ሆፕኪንስ ዩኒቨርስቲ መረጃ መሰረት እስካሁን ድረስ በአለማችን 108 ሚሊዮን ሰዎች በቫይረሱ ሲያዙ 2.3 ሚሊዮኖች ደግሞ ሞተዋል።