ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ኮሮናቫይረስ፡ የኦክስፎርድ ክትባት የኮሮናቫይረስ ስርጭትን እየቀነሰ መሆኑን ጥናቶች አመለከቱ
የኦክስፎርድ ክትባት የኮሮናቫይረስ ስርጭትን እየቀነሰ መሆኑን ጥናቶች አመለከቱ።
በኦክስፎርዱ አስትራዜኔካ ክትባት ላይ የተደረገው ጥናት የቫይረሱን ስርጭት እየቀነሰው መሆኑ በዩናይትድ ኪንግደም ጤና ሚንስትር በኩል ሙገሳን አስገኝቷል።
የዩናይትድ ኪንግደም የጤና ሚንስትር ማት ሃንኮክ "ከእዚህ ወረርሽኝ የመትረፊያ መንገዳችን ክትባት መሆኑን ጥናቱ አሳይቶናል" ብለዋል።
የቫይረሱን ስርጭት ክትባቱ መግታት እንደሚችል ሲረጋገጥ ይህ የመጀመሪያው ነው። ዩናይትድ ኪንግደም የመጀመሪያውን የኮሮናቫይረስ ክትባት ለ9 ነጥብ 6 ሚሊዮን ሰዎች ሰጥታለች።
ምንም እንኳ የተሟላ መረጃ ተጠናቅሮ የክትባቱ ስርጭትን የመግታቱ ውጤት ለህትመት ባይበቃም፣ ከተሰበሰቡት መረጃዎቨች በመነሳት ክትባቱ የቫይረሱን ስርጭት ከመግታት አኳያ ከፍተኛ ሚና ይኖረዋል ነው የተባለው።
ይህም ማለት ክትባቱን የወሰዱ ሰዎች ማስተላለፍ ስለማይችሉ በሌላ በኩል ሌሎች ሰዎችንም እየጠበቁ ነው ተብሎ ስለሚታሰብ የክትባቱ አስፈላጊነት ወሳኝ ሆኗል።
የጤና ሚንስትሩ ማት ሃንኮክ፣ ጥናቱን "እጅግ አበረታች" ያሉት ሲሆን በትዊተር ገጻቸው "ፍጹም የተሟላ" በማለት ውጤቱን ገልጸውታል።
ጥናቱ የተከናወነው ክትባቱን ባዘጋጀው ኦክስፎርድ ዩኒቨርሲቲ ሲሆን ምልክት የማይታይባቸው የቫይረሱ ተጠቂዎችን በመከታተል እና ሰዎች መቼ እንደሚታመሙ በመመዝገብ ተከናውኗል።
ስርጭትን በመግታት በኩል የታየው በጎ ዜና እንዳለ ሆኖ በአንድ ጊዜ ክትባት ብቻ ሰዎች 76 በመቶ ለሦስት ወር ከቫይረሱ መጠበቅ እንደሚችሉም ተረጋግጧል። በመሆኑም አደጋውን ለመቀነስ ተመራማሪዎች ሁለተኛው ዶዝ በ4 እና 12 ሳምንታት መካከል ቢወሰድ መልካም ነው የሚል ምክር አቅርበዋል።
ሁለተኛው የአስትራዜኔካ የክትባት ዶዝ ሲወሰድ የመከላከል አቅሙን 82 በመቶ እንደሚደርስ ጥናቶች ያመለክታሉ።
በሌላ በኩል ደግሞ በኮሮናቫይረስ ክትትል ከሚያደርጉ አንድ ዓለም አቀፋዊ ተቋማት መካከል አንዱ እንዳጠናው ከሆነ በኮሮናቫይረስ ተይዘው የዳኑ ሰዎች ከስድስት ወራት በኋላ 90 በመቶ የሚሆኑት ቫይረሱን የሚካላከል አንቲ ቦዲ [ጸረ ተህዋስ] ማዳበር እንደሚችሉ አረጋግጧል።
ዩናይትድ ኪንግደም ከሌሎች አገራት በተለየ መልኩ ለብዙ ሰዎች የመጀመሪያውን ክትባት ለመስጠት በሚል ሁለተኛውን ዙር እስከ 12 ሳምንታት በማዘግየት በርካታ ሰዎችን የመከተብ ሥራውን እያሳለጠች ነው።
አላማው ብዙ ሰዎችን በመከተብ የብዙ ሕይወት መታደግ የሚል ቢሆንም ዓለም አቀፍ ድጋፍ የለውም በሚል ከእንግሊዝ የጤና ማሕበር ዘንድ ተቃውሞ ገጥሞታል።
በኦክስፎርዱ የክትባት ሙከራ ውስጥ ከፍተኛ ተመራማሪ የሆኑት ፕሮፌሰር አንድሪው ፖላርድ ግን ዩናይተድ ኪንግደም የምትሄድበት መንገድ አዋጭ ነው በማለት ድጋፋቸውን ሰጥተዋል።