ግዙፉ የአውስትራሊያው የስፖርት ክለብ “ዘረኛ” ነው ተባለ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በአውስራሊያ ሊግ ተሳታፊ ከሆኑት ክለቦች መካከል አንዱ እና ግዙፉ ኮሊምግዉድ “ዘረኛ የሆነ ስርዓትን ዘርግቷል” ሲል አንድ ገለልተኛ አጣሪ ቡድን አጋለጠ።
ይህ ገለልተኛ አጣሪ ቡድን ይፋ ባደረገው ሪፖርት እንዳተተው ይህ ግዙፍ የራግቢ ቡድን ዘረኝነትን በተመለከተ ለሚነሱ ቅሬታዎች ምላሽ ለመስጠት ፍላጎት የለውም ከፍ ሲልም ቅሬታ በሚያነሱት ላይ ቅጣት ያስተላልፋል ብሏል።
ሪፖርቱን ተከትሎ ግዙፉ ክለብ “የተሻለ ለመሆን እጥራለሁ” ብሏል።
የክለቡ ፕሬዝደንት ክለቡ ጥፋተኛ መሆኑን አምነው ጸረ-ዘረኛ የሆኑ ፖሊሲዎችን በማርቀቅ የተሻለ ስፍራ ለመሆን እሰራለሁ ብሏል።
ጥናቱ ይፋ እንዳደረገው ከሆነ የዘር መድሎ ደርሶብኛል ከሚል ስፖርተኛ ይልቅ ዘረኝነትን በተመለከተ በመገናኛ ብዙሃን ለሚነሱ ጥያቄዎች ክለቡ ምላሽ ይሰጣል፣ እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ ዘረኝነትን ለመከላከል ክለቡ ምንም አይነት ስትራቴጂ አልነበረውም፤ እንዲሁም ዘረኝነትን በተመለከተ በክለቡ ሲወሰዱ የነበሩ እርምጃዎች ተጎጂውን ሳይሆን የክለቡን ስምእና ዝና ለመጠበቅ ያለመ ነው።
ይህ የጥናት ውጤት ይፋ የተደረገው ገለልተኛ ጥንት አድራጊ ቡድኑ ተጫዋቾችን፣ የክለቡ ሰራተኞችን እና ደጋፊዎችን ካነጋገረ በኋላ ነው።
በዚህ ጥናት ላይ የቀድሞ የክለቡ ተጫዋች ሄሪቲኤር ሉሙምባ በክላቡ አጋጥሞኛል ስላለው ጉዳይ ተሞክሮውን አጋርቷል።
የዘር ሃረጉ ከብራዚል እና አንጎላ የሚመዘዘው ተጫዋች የቡድን አባላቶቹ ‘ቺምፕ’ (ቺምፓዚ) በሚል ስም ይጠሩት እንደነበረ ተናግሯል።
የቀድሞ የክለቡ ተጫዋች ሉሙምባ ክለቡን ኮሊንግውድ እና የአውስትራሊያ ሊግን ለመክሰስ በዝግጅት ላይ መሆኑን አስታውቋል።
የአውስትራሊያው ራግቢ ሊግ በርካታ ተመልካቾች ያሉት ሊግ ሲሆን በሊጉ ውስጥ ዘረኝነትን ለመከላከል የተለያዩ ጠንካራ እርምጃዎችችን እንደሚወስድ አስታውቋል።












