የናይጄሪያው ሼል ላደረሰው ብክለት ለአርሶ አደሮች ካሳ እንዲከፍል ተወሰነበት

የተበከለ ውሃ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ታትሟል

የኔዘርላንድስ ፍርድ ቤት በኒጀር ዴልታ ተፋሰስ የነዳጅ ብክለት አስከትሏል በሚል በናይጄሪያ የሚገኘውን የሼል ኩባንያ ቅርንጫፍ ጥፋተኛ አድርጎታል፤ ካሳም እንዲከፍል አዞታል።

ፍርድ ቤቱ የናይጄሪያው ሼል ጉዳት ለደረሰባቸው ናይጄሪያዊ አርሶ አደሮች ካሳ እንዲከፍል እንዲሁም ተቋራጩ የሆነው የእንግሊዙ-ደች ኩባንያ ለወደፊቱ የሚፈጠርን ጉዳት ለመከላከል አስፈላጊ የሚባለውን ቁሳቁስ እንዲገጥም ትዕዛዝ ተላልፎለታል።

በአውሮፓውያኑ 2008 ሼል አካባቢያችንን በክሎታል በሚል አርሶ አደሮቹ ክስ መመስረታቸው ይታወሳል።

ሼል በበኩሉ "ሆን ብሎ የተጠነሰሰብኝ ሴራ ነው" ይላል። በዛሬው እለት የደች ሼል ባወጣው መግለጫ በውሳኔው "አዝነናል"ብሏል።

ኩባንያው ይግባኝ የመጠየቅ መብት አለው ተብሏል።

ፍርድ ቤቱ በበኩሉ "ጎይና ኦሩማ በሚባሉ መንደሮች ላይ ነዳጁ ፈስሶ ለደረሰው ጉዳት ኩባንያው ሴረኞች የፈፀሙት ነው ቢልም ማስረጃ ማቅረብ አልቻለም። ኩባንያው ከነበረው ደካማ አሰራር ጋር የተያያዘ ነው" ብሏል ችሎቱ።

"በነዚህ አካባቢዎች ተንጠባጥቦና ፈስሶ ለደረሰው ብክለትና ጉዳት ሼል ናይጄሪያ ተጠያቂ ነው" በማለት ፍርድ ቤቱ አስምሯል።

የካሳው መጠንም ከዚህ በኋላ የሚወሰን ይሆናል።

ኢኮት አዳ ኡዶ በተባለው መንደር ኩባንያው እንዳለው ሆን ተብሎ የተፈፀመ ለመሆኑ አንዳንድ ፍንጮች በመኖራቸው የበለጠ እመረምረዋለሁ በማለት ፍርድ ቤቱ ለጊዜው ይዞታል።

ከሳሾቹ አራት አርሶ አደሮች ከመሬት ስር የተቀበረው የነዳጅ ማስተላለፊያ ቧንቧ ፈስሶ ውሃቸው እንዲሁም መሬታቸው እንደተበከለና መላ ህይወታቸውን ግልብጥብጡን እንዳወጣው ገልፀዋል። ከከሳሾቹ ውስጥ ሁለቱ መሞታቸውን አጃንስ ፍራንስ ፕሬስ በዘገባው አስነብቧል።

አርሶ አደሮቹን ፍሬንድስ ኦፍ ዘ ኧርዝ የተባለ የከባቢ ጥበቃ ቡድን ደግፏቸዋል።

"የደስታ እንባ ነው የማነባው፤ ከአስራ ሶስት አመታት በኋላ አሸነፍን" በማለት የቡድኑ ኔዘርላንድስ ቅርንጫፍ ተወካይ በውሳኔው የተሰማቸውን ደስታ በትዊተር ገፃቸው አስፍረዋል።

በዛሬው እለት የተላለፈው ውሳኔ ከናይጄሪያ አልፎ የኩባንያዎች ኃላፊነት እስከምን ድረስ ሊሆን ይገባል በሚለው ጉዳይ ላይ ሌሎች አገራት ላይ ተፅዕኖ ሊያሳድር ይችላል ተብሏል።

በዚህ ክስ ላይ የነዳጁ ፍሰት የተፈጠረው ከ2004-2007 ቢሆንም በአሁኑም ወቅት በኒጀር ደልታ ከነዳጅ መተላለፊያ ቧንቧዎች የሚወጣው ብክለት ትልቅ ችግር ነው ተብሏል።