አሜሪካ፡ የትራምፕ ነውጠኛ ደጋፊዎች እንደተፈሩት እየበጠበጡ አይደለም ተባለ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ጆ ባይደን ወደ ነጩ ቤተ መንግሥት ለመግባት ደጅ በቆሙበት ሰዓት በአሜሪካ በርካታ ግዛቶች የትራምፕ ደጋፊዎች አገሪቱ ላይ ነውጥ ይቀሰቅሳሉ ተብሎ ተፈርቶ ነበር፡፡
ሆኖም የተፈራው እስከአሁን አልደረሰም፡፡
የተወሰኑ በቁጥር የተመናመኑ ደጋፊዎቻቸው ግን ትናንትና እሑድ በዲሲ ወዲያ ወዲህ ሲሉ ታይተዋል፡፡ የተወሰኑትም መሣሪያ የታጠቁ ነበሩ፡፡
ከዲሲ ሌላ በቴክሳስ ኦረገን፣ በሚቺጋን ኦሃዮና ሌሎች ቦታዎች የትራምፕ ነውጠኛ ደጋፊዎች በትንሹ ቁጥር ተሰባስበው ታይተዋል፡፡
ከነገ በስቲያ ረቡእ የፕሬዝዳንታዊ ቃለ መሐላ ሥነ ሥርዓት የሚያደርጉት 46ኛው ተመራጭ ፕሬዝዳት ጆ ባይደን ቃለ መሐላ ከመፈጸማቸው በፊት ከፍ ያለ ነውጥ ሊኖር ይችላል ሲል የአሜሪካ የወንጀል ምርመራ ቢሮ (FBI) ስጋቱን ገልጾ ነበር፡፡
ጆ ባይደን ነጩ ቤተ መንግሥት እየገቡ ያሉት የትራምፕ ደጋፊዎች ካፒቶል ሒልን ከደፈሩ ከሁለት ሳምንት በኋላ መሆኑ ነው፡፡
በዚህ ነውጥ 5 ሰዎች መገደላቸው ይታወሳል፡፡ ከሟቾቹ መካከል አንዱ የፖሊስ መኮንን ነው፡፡
ይህን ነውጥ በበላይነት የመሩትና ያስተባበሩት ፕሬዝዳንት ትራምፕ መሆናቸው በመታመኑም በአሜሪካ ታሪክ በግዛት ዘመኑ 2ጊዜ የተከሰሰ ብቸኛ ፕሬዝዳንት ለመሆን በቅተዋል፡፡
የጆ ባይደንን የቃለ መሐላ ሥነ ሥርዓትን ከአደጋ ለመጠበቅ 25ሺ የሚሆኑ የናሽናል ጋርድ ልዩ ሠራዊት አባላት በመላው ዋሺንግተን ተሰማርተዋል፡፡
የዚህ ልዩ ኃይል መሪ ራየን ማከቴ ለአሶሲየትድ ፕሬስ እንዳሉት አባላቱ የትራምፕ ነውጠኛ ደጋፊ አጋዦች እንዳይሆኑ ጥንቃቄ ለማድረግም ቅድመ ምርመራ ቢጤ ተደርጎባቸዋል ብለዋል፡፡
ለምሳሌ ትናንት እሑድ አንድ የኒው ሜክሲኮ ግዛት የአካባቢ አስተዳዳሪ በዋሺንግተን በቁጥጥር ሥር ውሏል፡፡ ባለሥልጣኑ በቁጥጥር ሥር የዋለው ከጃንዋሪ 6ቱ የካፒቶል ሒል ጋር በተያያዘ ነው፡፡
ከነውጠኛ የትራምፕ ደጋፊዎች መካከል ካውቦይስ የሚባሉት በቃለ መሐላው ሥነ ሥርዓት ወቅት ወደ አደባባይ ተመልሰው እንደሚፋለሙ ሲዝቱ ነበር፡፡
በርካታ የአሜሪካ ከተሞች ስጋት ስለያዛቸው ከወዲሁ ሰራዊት ማሰማራት ጀምረዋል፡፡
ትራምፕን የሚያደንቁና የነጭ የበላይነት የሚሰብኩ የኢንተርኔት ቡድኖች ደጋፊዎቻቸው በየከተማው አደባባይ እንዲወጡ እየቀሰቀሱ ይገኛሉ፡፡
አንዳንድ ቡድኖች ግን የልዩ ኃይል መሰማራትን ተከትሎ ተቃውሟቸውን እየሰረዙ ይገኛሉ፡፡
ኒውዮርክ ታይምስ እንደዘገበው 25 የሚሆኑና የታጠቁ አደገኛና ነውጠኛ የቡጋሎ ቦይስ አባላት በኮለምበስ ኦሃዮ ታይተዋል፡፡
በሚቺገን ቁጥራቸው ጥቂት የሆኑ የትራምፕ ደጋፊዎች ጠመንጃ ይዘው አደባባይ ወጥተው የነበረ ሲሆን ጉዳት ሳያደርሱ ወደቤታቸው ተመልሰዋል፡፡
ተመሳሳይ ቁጥር ያላቸው የትራምፕ ደጋፊዎች ትናንት እሑድ በቴክሳስ ኦስቲን፣ እንዲሁም በፔኒሲልቬኒያ ሐሪበርግ ተስተውለዋል፡፡
ነውጠኞቹ የትራምፕ ደጋፊዎች ከነገ በስቲያ እሑድ በብዙ ቁጥር ሊወጡ ይችላሉ የሚለው ፍርሃት ግን አሁንም አለ፡፡
ባይደን ሐሙስ ዕለት ከስልጣናቸው በ24 ሰዓት ውስጥ የትራምፕን ከሙስሊም አገራት የጉዞ ክልከላን ያነሳሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡
አሜሪካንን ወደ ፓሪስ የአየር ንብረት ስምምነትንም ይመልሳሉ ተብሎ እየተጠበቀ ነው፡፡
ሜክሲኮ ድንበር ላይ ከወላጆቻቸው የተለያዩ ሕጻናትንም እንዲገናኙ እንደሚፈቅዱ ተዘግቧል፡፡
የባይደን ቡድን አሜሪካዊያን ለቃለ መሐላ ሥነ ሥርዓቱ ወደ ዋሺንግተን ጉዞ እንዳያደርጉ ተማጽነዋል፡፡ ዋናው ምክንያት ግን የትራምፕ ደጋፊዎች ነውጥ ፍርሃት ሳይሆን የኮቪድ ተህዋሲ እንዳይስፋፋ ነው፡፡












