ግብጽ 3ሺ ዓመታት ያስቆጠረ ግዙፍ ቤተ መቅደስና መካነ መቃብር አገኘች

የፎቶው ባለመብት, EPA
የመሬት ውስጥ የተቀበሩ ቅርሶች ጥናት ቡድን (Archaeologists) በግብጽ አስደናቂ የሚባል መካነ መቃብርና ቤተ መቅደስ ፈልፍለው አግኝተዋል፡፡
የመቃብር ሥፍራውና ቤተ መቅደሱ ግዙፍና 3ሺ ዓመታትን ያስቆጠረ ነው ተብሏል፡፡
ይህ አስደናቂ ግኝት ከመሬት በታች ተቀብሮ የተገኘው በደቡባዊ ካይሮ ሰቃራ ተብሎ በሚጠራው መንደር ነው፡፡
ከ50 በላይ ሬሳዎች በጥንታዊ የግብጾች ሬሳን አድርቆ የማቆየት ጥበብ በቤተ መቅደሱ ተቀብረው ተገኝተዋል፡፡
ከ50ዎቹ መቃብሮች መሀል አንዱ የሥርወ መንግሥቱ ወታደር እንደነበረ የተገመተ ሲሆን ከጦር መሣሪያዎቹ ጋር ነው ተቀብሮ የተገኘው፡፡ መጥረቢያው አብሮት ተቀብሮ ይታያል፡፡
በቤተ መቅደሱ ከተቀበሩ ነገሮች መካከል የእንጨት ታንኳዎችና የፓፒረስ ጽሑፎች ልዩ ትኩረት አግኝተዋል፡፡
ይህ በፓፒረስ የተጻፈው ጽሑፍ አንድ ምዕራፍ "book of the dead" በመባል ከሚታወቀው መጽሐፍ የተቀዳ ነው፡፡
ከደረቁ ሬሳዎች መሀል ፈርኦኖች ከሞቱ በኋላ ባለው ሕይወታቸው ሊጫወቱባቸው የሚችሉ የተለያዩ ጊዜ ማሳለፍዎች (Games) መገኘታቸው ለተመራማሪዎች ትልቅ ፈንጠዚያን የፈጠረ ሆኗል፡፡
የዚህ የቁፋሮ ጥናት ባለሙያ መሪ እንዳብራሩት ታሪካዊ ሰነዶች እንደሚያስረዱት ይህ ‹ሰኔት› በሚባለውና ከሞት በኋላ ይደረጋል ተብሎ በሚታመነው የጨዋታ ውድድር (ጌም) ያሸነፉት ሟቾች ወደ ገነት ይገባሉ ተብሎ ይታመን ነበር፡፡
እነዚህ በቤተ መቅደሱ ውስጥ የተገኙት ሬሳዎችና ቁሳቁሶች በትንሹ 3ሺ ዓመት ዕድሜ እንዳስቆጠሩ ተረጋግጧል፡፡
በብዛት ከተገኙት ቁሳቁሶች መሀል የፊት ጭምብሎች፣ ትንንሽ ሀውልቶችና አሻንጉሊቶች እንዲሁም ታንኳዎች ይገኙበታል፡፡
በቤተ መቅደሱ ውስጥ የንጉሥ ቴቲ ሚስት የነበረችው ንግሥት ናአርት መገማሸሪያዎች ተገኝተዋል፣ ከሸክላ የተሰሩ 3 መጋዘኖችም አብረውት አሉ፡፡
ሳቃራ የግብጽ ጥንታዊ ከተማ የሆነችው መምፊስ አካል ስትሆን ጊዛን እና ፒራሚዶቹ የሚገኙበትን ስፍራ ይጨምራል፡፡

የፎቶው ባለመብት, EPA
ይህ ስፍራ ከ1970ዎቹ ጀምሮ ዩኒስኮ የሚያውቀው ከዓለም አስደናቂ ቅርሶች ተርታ በግንባር ቀደምትነት የሚጠራ ነው፡፡
የዚህ ቤተ መቅደስና መካነ መቃብር መገኘት ግብጽ ሆስኒ ሙባረክን ካስወገደች በኋላ ተቀዛቅዞ የነበረውን የቱሪዝም ዘርፍ በከፍተኛ ሁኔታ ያነቃቃል ተብሎ ተምኗል፡፡
ግብጽ በዚህ ዓመት መጨረሻ በጊዛ ኮረብታማ ሥፍራ እጅግ ግዙፉን የግብጽ ታላቁን ሙዝየም ለሕዝብ ይፋ ታደርጋለች ተብሎ እየተጠበቀ ነው፡፡
ለግብጽ ምጣኔ ሐብት የጀርባ አጥንት የሆነው ቱሪዝም ከአልሲሲ ቆራጥ አመራር በኋላ ቀስ በቀስ እያንሰራራ እንደሚገኝ ይነገራል፡፡
ግብጽ በዓለም ከፍተኛ ቁጥር ያለው ቱሪስት ከሚጎርፍላቸውና ጥንታዊ ሥልጣኔን ከታደሉ አገራት ተርታ የምትመደበት ናት፡፡
ግብጽ ባለፈው ኅዳር ከ100 በላይ ደርቀው በወጉ የተቀመጡ ሬሳዎችን ከመካነ መቃብር ማግኘቷ ይታወሳል፡፡
እነዚህ ሬሳዎች ግብጽን ከክርስቶስ ልደት በፊት በ300 ዓመተ ዓለም አካባቢ የመሩ የቶሌማይክ ሥርወ መንግሥት አባላት የሚገኙባቸው እንደሆኑ ተደርሶበታል፡፡
መቶዎቹ ሬሳዎች የተገኙትም ከዚሁ ሳቃራ ከሚባለው ጥንታዊ መንደር ነው፡፡












