አርሚን ላሼት የአንጌላ መርክል ሲዲዩ ፓርቲ ሊቀመንበር ሆነው ተመረጡ

የፎቶው ባለመብት, Reuters
አርሚን ላሼት የጀርመኗ መራሔተ መንግሥት አንጌላ መርክል ፓርቲ ለሆነው ክርስቲያን ዲሞክራት ሕብረት [ ሲዲዩ] ሊቀመንበር ሆነው ተመረጡ።
የሰሜን ርሂን ውስትፓሊያ ግዛት ጠቅላይ ሚኒስትር የሆኑት ላስሼት ቨርቹዋል በተካሄደ የፓርቲው ስብሰባ ነው ሁለት ተፎካካሪያቸውን ያሸነፉት።
16 ዓመታት ሥልጣን ይዘው የቆዩት አንጌላ መርክል በመጭው መስከረም ወር ሥልጣናቸውን ሲለቁ ለመተካት ጥሩ አቋም ላይ ይገኛሉም ተብሏል።
ይሁን እንጂ የኮቪድ -19 ወረርሽኝን ተከትሎ በርካታ ፖለቲካዊ ተግዳሮቶች ይገጥሟቸዋል።
የ59 ዓመቱ ላሼት ወግ አጥባቂውን የቢዝነስ ሰው ፍሬድሪክ መርዝ 521 በሆነ ድምፅ ያሸነፉ ሲሆን፤ ሦስተኛው እጩ ኖርበርት ሮትገን ደግሞ በመጀመሪያው ዙር ውድድር ተሰናብተዋል።
በዚህም መሠረት ላሼት ከሁለት ዓመታት በፊት የተሾሙትን የፓርቲው መሪ የነበሩትን አኔግሬት ክራምፕ ካሬንቦርን ይተካሉ።
ጀርመን መስከረም ላይ ምርጫ የምታካሂድ ሲሆን፤ የሲዲዩ ፓርቲ ሊቀመንበር ለመራሔ መንግሥትነት እጩ ተወዳዳሪ ለመሆን ምንም ዋስትና የለውም።
የላሼት ምክትሎች ሆነው ከተመረጡት አንዱ የጤና ሚኒስትር ጀንስ ስፓን እና የሲዲዩ ባቫሪያን እህት ፓርቲ ሲኤስዩ መሪ ማርከስ ሶደርም ኃላፊነቱን ስለመፈለጋቸው ባይገልፁም፤ ወደ ውድድሩ ቀለበት ግን መግባት ችለዋል።
የመጨረሻው ውሳኔያቸው በመጪው ፀደይ ወቅት ይታወቃል ተብሏል።
ላሼት የአንጌላ መርክል ታማኝ ደጋፊ ናቸው።












