ትራምፕ ሥልጣን ከመልቀቃቸው ከጥቂት ቀናት በፊት የመጨረሻው የሞት ቅጣት ተፈጸመ

ታትሟል

በአሜሪካዋ ግዛት ኢንዲያና ውስጥ የሞት ፍርደኛ የነበረው እስረኛ ደስቲን ሂግስ በፕሬዝዳንት ትራምፕ የሥልጣን ዘመን የመጨረሻው ሞተ የተፈጸመበት ግለሰብ ሆኗል።

ሂግስ ከ25 ዓመት በፊት በዱር እንስሳት መጠለያ ውስጥ ሦስት ሴቶች ላይ በተፈፀመ የግድያ ወንጀል ጥፋተኛ የተባለ ሲሆን፤ ግለሰቡ የሞት ፍርዱ ተግባራዊ አስከሆነበት ጊዜ ድረስ ግድያውን ማዘዙን ሲያስተባብል ቆይቷል።

ግለሰቡ አርብ ለቅዳሜ ሌሊት በመርዝ መርፌ ተወግቶ የሞት ፍርዱ ተፈጻሚ ሆኖበታል።

ግድያው የአሜሪካ መንግሥት በፌደራል ግድያዎች ላይ ለ17 ዓመታት ጥሎት የነበረውን ዕገዳ ካነሳበት ካለፈው ሰኔ ጀምሮ የተካሄደው 13ኛው የሞት ቅጣት ነው።

ውሳኔው ተግባራዊ የተደረገው የሞት ፍርድን የሚቃወሙት ተመራጩ ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ቃለ መሃላ ሊፈጽሙ ጥቂት ቀናት ሲቀሩ ነው።

አዲስ ፕሬዝዳንት ተመርጦ ሽግግር በሚካሄድበት ወቅት ላለፉት 130 ዓመታት የሞት ቅጣቶች የማይፈጸሙበት ጊዜ እንደሆነ በልማድ ይታወቅ ነበር።

ነገር ግን የትራምፕ አስተዳደር ይህንን የቆየ ልማድን በመጣስ በፕሬዝዳንታዊ ሽግግር ወቅት የሞት ቅጣቱን ለመፈፀም በመጣደፉ ትችቶች ተሰንዝረውበታል።

ደስቲን ሂግስ በምን ተከሰሰ?

ወንጀለኛው ሂግስ ከሃያ ዓመታት በፊት ታንጂ ጃክሰን፣ ታሚካ ብላክ እና ሚሻን ቺን በተባሉ ሴቶች ላይ የተፈጸመውን አፈናና ግድያን በመምራት ጥፋተኛ ተብሎ የሞት ፍርድ ተወስኖበታል።

ወንጀሉ በአንድ አፓርታማ ከሂግስ እና ከሌሎች ሁለት ወንዶች ጋር በነበሩበት ጊዜ ከሟች ሴቶቹ ጋር መግባባት ሳይችሉ ይቀራሉ።

ሂግስና ተባባሪው ዊሊስ ሄይንስ ወደ ቤታቸው እንደሚወስዷቸው ቢነግሯቸውም በምትኩ ሜሪላንድ ወደሚገኘው የዱር እንስሳት መጠለያ ወስደዋቸዋል። ዐቃቤ ሕጎች እንደሚሉት ሂግስ ለሄይንስ ጠመንጃ እንደሰጠውና ሦስቱን ሴቶች እንዲመታቸው ትዕዛዝ አስተላልፏል።

ተኳሽ ነበርኩ ብሎ ያመነው ሄይነስ በተለየ ችሎት የዕድሜ ልክ እስራት ተፈረዶበታል።

ለፕሬዚዳንት ትራምፕ በቀረበው የምህረት ጥያቄ ጠበቃው "ሂግስን ከዋነኛው ገዳይ በከፋ ሁኔታ መቅጣት የዘፈቀደ እና ኢፍትሃዊ ነው" ብለዋል።

ፍርድ ቤት ሂግስና ለሌላ ኮሪ ጆንሰን የተባለ እስረኞች በኮቪድ-19 በመያዛቸው ጠበቆቻቸው ፍርዱ አፈጻጸም እንዲዘገይ ትዕዛዝ ተሰጥቶ ነበር። ነገር ግን በቀረበው የይግባኝ ጥያቄ መሠረት ውሳኔው ተቀልብሶ ቅጣቱ ተግባራዊ ሆኗል።

የሂግስን የሞት ፍርድ ለማስቆም የተደረገው የመጨረሻ ሙከራ አርብ ዕለት በዩናይትድ ስቴትስ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ውድቅ ሆኖ ውሳኔው ተግባራዊ ሆኗል።

የሕግ ባለሙያዋ ሶንያ ሶቶሜየር ውሳኔውን በመቃወም "ይህ ፍትህ አይደለም" ሲሉ ጽፈዋል። "የፌዴራል የሞት ቅጣትን ለመቀጠል ለሁለት አስርት ዓመታት ያህል ከቆየ በኋላ መንግስት በሕግ አግባብ መፈጸሙን ማረጋገጥ ነበረበት። ይህም አልሆነም" ብለዋል።

ከሐምሌ ወር ጀምሮ የሞት ፍርድ ተግባራዊ የተደረገባቸውን የ13 ሰዎችን ስሞች ዘርዝረዋል። "ከታሪክ አንፃር ለማስረዳት የፌዴራል መንግሥቱ ባለፉት ስድስት አሥርት ዓመታት ከተፈጸመው ከሦስት እጥፍ በላይ ሰዎችን በሞት ቀጥቷል" ብለዋል።

ሂግስ የሞት ቅጣቱ ተግባራዊ ከመሆኑ በፊት በሰጠው የመጨረሻ ኑዛዜው ንፁህ መሆኑን በድጋሚ ተናግሯል።

ሦስቱን ሴቶች በስም በመጥቀስ "እኔ ንፁህ ሰው ነኝ። ግድያውን አላዘዝኩም" ብሏል።

ሂግስ በፌዴራል የሞት ፍርድ ላይ የነበረችውን ብቸኛዋን ሴት ሊሳ ሞንትጎምሪንና በዚህ ሳምንት ኢንዲያና ውስጥ ቴር ሀውት በሚባል የፌደራል እስር ቤት የሞት ቅጣቱ የተፈጸመበትን ግለሰብ ጨምሮ ሦስተኛው ነው ተብሏል።

ከሂግስ ጠበቆች መካከል አንዱ የሆኑት ሾን ኖላን በሰጠው መግለጫ "መንግሥት በማርቲን ሉተር ኪንግ የልደት ቀን ማንንም ያልገደለውን ጥቁሩን ደስቲን ሂግስን ጨምሮ 13 የሰው ልጆች በመግደል ተጠናቋል" ብሏል።