ኮሮናቫይረስ ፡ ለአባል አገራቱ የሚቀርበው የፋይዘር የኮቪድ-19 ክትባት ዘገየ ያለው የአውሮፓ ሕብረት ቁጣውን አሰማ

አንዲት የህክምና ባለሙያ ፈረንሳይ ውስጥ ክትባቶችን ስታዘጋጅ

የፎቶው ባለመብት, EPA

የምስሉ መግለጫ, አንዲት የህክምና ባለሙያ ፈረንሳይ ውስጥ ክትባቶችን ስታዘጋጅ
ታትሟል

የአሜሪካው መድኃኒት አምራች ድርጅት ከሚፈለገው ቁጥር በታች ክትባቶችን እየላከ በመሆኑ በርካታ የአውሮፓ ሕብረት አገራት የፋይዘር የኮሮናቫይረስ ክትባት በጣም አነስተኛ መጠን እየደረሳቸው ነው።

ስድስት የሕብረቱ አገራት ሁኔታውን "ተቀባይነት የለሌው" እና "የክትባቱን ሂደት ተአማኒነት የሚቀንስ" ነው ሲሉ አስጠንቅቀዋል።

ስዊድን፣ ዴንማርክ፣ ፊንላንድ፣ ሊቱዌንያ፣ ላቲቪያ እና ኢስቶኒያ የአውሮፓ ሕብረት በፋይዘር-ባዮኤንቴክ ላይ ጫና እንዲያደርግም አሳስበዋል።

የአቅርቦቱ አነስተኛ መሆን ጊዜያዊ ችግር እንደሆነ ፋይዘር አስታውቋል።

የመድኃኒት አምራቹ አርብ ዕለት በሰጠው መግለጫ ምርቱን ለማሳደግ በተደረጉ የምርት ሂደቶች ምክንያት በአቅርቦት ላይ ችግር መከሰቱን ገልጿል።

"ምንም እንኳን ይህ ከጥር መጨረሻ እስከ የካቲት መጀመሪያ ድረስ ለጊዜው በአቅርቦት ላይ ተጽዕኖ የሚያሳድር ቢሆንም፣ ከየካቲት መጨረሻ ጀምሮ የሚቀርበው ክትባት በከፍተኛ መጠን እንዲጨምር ያደርጋል" ብሏል።

ኩባንያው የምርት ማሻሻያ ክትባቶችን ወደ ዩናይትድ ኪንግደም (ዩኬ) በማድረስ ረገድ ላይም "የአጭር ጊዜ ተፅእኖ" እንደሚኖረው ገልጿል።

የዩኬ መንግሥት ግን እስከ የካቲት አጋማሽ ድረስ 15 ሚሊዮን የሚደርሱ ቅድሚያ የሚሰጣቸው ሁሉም የማኅበረሰቡ ክፍሎችን የመከተብ ግቡን ለማሳካት ማቀዱን ገልጿል።

በዩኬ ውስጥ ከፋይዘር በተጨማሪ የኦክስፎርድ ዩኒቨርሲቲ እና የአስትራዜኔካ ክትባቶችም እየተሰጡ ይገኛል።

የአውሮፓ ሕብረት በአሜሪካው ኩባንያ ሞዴርና የተሰራውን ክትባት ሥራ ላይ እንዲውል በማፅደቁ በፋይዘር ላይ ሙሉ በሙሉ ጥገኛ አይደለም። ቢሆንም የክትባት መርሃ ግብሮቹን ፍጥነት ይቀንሰዋል ተብሎ ይጠበቃል።

የጀርመን ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር እስከ የካቲት አጋማሽ ድረስ የክትባት አቅርቦቱ እንደሚዘገይ መነገሩ የተገባውን ቃል በመጥቀስ የፋይዘርን ውሳኔ "አስገራሚ እና አሳዛኝ ነው" ብሎታል።

የአውሮፓ ሕብረት ኮሚሽን ፕሬዝዳንት ኡርሱላ ቫን ደር ሌን በዓመቱ የመጀመሪያ ሩብ ክፍል ሁሉም ትዕዛዞች እንደሚደርሱ ከፋይዘር ዋና ሥራ አስፈፃሚ በኩል ማረጋገጫ እንደተሰጣቸው ተናግረዋል።

ቫን ደር ሌን ባለፈው ሳምንት እንዳሉት ፋይዘር የመጀመሪያ ትዕዛዙን በእጥፍ በማሳደግ በዚህ ዓመት ለአውሮፓ ሕብረት 600 ሚሊዮን የክትባት ጠብታዎች ለማቅረብ መስማማቱን ገልጸዋል።

ውሳኔው በዩኬ ውስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ የተገኘውና በፍጥነት የሚያሰራጨውን የኮቪድ-19 አዲስ የቫይረስ ዝርያ ለመከላከል የሚታገሉትን የአውሮፓ መንግሥታት የሚያረጋጋ አይመስልም።

ከ27ቱ የአውሮፓ ሕብረት አባል መንግሥታት ውስጥ አንድ ሦስተኛ የሚሆኑት በዚህ ሳምንት በተካሄደ ስብሰባ ላይ "በቂ" ክትባት እንዳላገኙ ሪፖርት ማድረጋቸውን ሮይተርስ አንድ ተሳታፊን ጠቅሶ ዘግቧል።

ሊቱዌንያ እስከ የካቲት አጋማሽ ድረስ ቃል ከተገባው ግማሽ ያህሉን የፋይዘር ክትባት ብቻ እንደምታገኝ ተናግራለች።

ቤልጅየም በበኩሏ በጥር ወር ከታቀደው ግማሽ ያህሉን እቀበላለሁ ብላ እንደምትጠብቅ ገልፃለች። ካናዳ ያዘዘቸው ክትባት የሚመጣው ቤልጅየም ውስጥ ከሚገኘው የፋይዘር ፋብሪካ ስለሆነ አቅርቦቷ ይስተጓጎላል ተብሏል።

የአውሮፓ ሕብረት አባል ያልሆነችው ኖርዌይ አርብ ዕለት ፋይዘር እስከ መጪው ሳምንት ድረስ ለአገሪቱ የሚያቀርበውን የክትባት መጠን ለጊዜው እየቀነሰ መሆኑን ገልፃለች።

የአውሮፓ ሕብረት የትኞቹን ክትባቶች እየገዛ ነው?

የአውሮፓ ኮሚሽን ክሊኒካዊ ሙከራዎችን ካጠናቀቁ በኋላ በመቶ ሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ክትባቶችን ለመግዛት ከፋይዘርባዮኤንቴክ በተጨማሪ ከአምስት ሌሎች የመድኃኒት አምራች ኩባንያዎች ጋር የተለያየ መጠን ያለው ክትባት ለመግዛት ስምምነት ላይ ደርሷል።

በዚህም መሠረት

  • ከአስትራዛኔካ = 400 ሚሊዮን
  • ከሳኖፊ-ጂ ኤስ ኬ = 300 ሚሊዮን
  • ከጆንሰን ኤንድ ጆንሰን = 400 ሚሊዮን
  • ከኩሬቫክ = 405 ሚሊዮን
  • ከሞዴርና = 160 ሚሊዮን

በተጨማሪም ኮሚሽኑ ከኖቫቫክስ እስከ 200 ሚሊዮን የሚደርሱ ክትባቶችን ለመግዛት የመጀመሪያ ዙር ንግግሮችን አጠናቋል።