ኮሮናቫይረስ፡ በሰመመን ውስጥ እያሉ የተመረጡት የብራዚሉ ከንቲባ በኮቪድ-19 ሞቱ

ከንቲባ ማጉይቶ ቪየላ

የፎቶው ባለመብት, Ciro Gomes Twitter

ታትሟል

የብራዚሏ ጎያኒያ ከተማ በኮቪድ-19 ህይወታቸው ያለፈው ከንቲባዋ ማጉይቶ ቪየላ ምክንያት በሃዘን ተውጣለች።

ፖለቲከኞችና ከንቲባው በህይወት እያሉ ይደግፉት የነበረው የእግር ኳስ ክለብ ተጫዋቾችም ሃዘናቸውን በማህበራዊ ሚዲያዎች ላይ እየገለፁ ነው።

በህዳር ወር የተመረጡት ማጉይቶ ቪየላ በወቅቱም በፅኑ ህሙማን ክፍል በማገዣ መሳሪያ (ቬንትሌተር) እርዳታ ላይ ነበሩ ተብሏል።

ምርጫውን ማሸነፋቸውን ወዲያው ያላወቁት ከንቲባው ከሰመመን ሲነቁም ልጃቸው እንደነገራቸው ተነግሯል።

የ71 አመቱ ማጉይቶ ቪየላ በኮሮናቫይረስ ህመም ወደ ሆስፒታል የተወሰዱት በጥቅምት ወር ነበር።

ቤተሰባቸውም በኮሮናቫይረስ ከፍተኛ ጉዳት ከደረሰባቸው መካከል ናቸው። የከንቲባው ታላቅ ሁለት እህቶች በኮሮናቫይረስ ሞተዋል። ግለሰቦቹ በአስር ቀናት ልዩነትም ህይወታቸውን እንዳጡ ተዘግቧል።

ከአሜሪካ ቀጥሎ በኮሮናቫይረስ ሟቾች ቁጥር እየተከተለች ባለችው ብራዚል 205 ሺህ ዜጎቿን በቫይረሱ ተነጥቃለች።

በብራዚሏ ማናውስ ከተማ የሚገኙ ሆስፒታሎች ለኮሮናቫይረስ ህሙማን የሚውል የማገዣ መሳሪያ መተንፈሻ (ኦክስጅን) ከፍተኛ እጥረት እንዳጋጠማቸውና ተስፋ አስቆራጭ ሁኔታም ላይ ደርሷል ተብሏል።

ከተማዋ በኮሮና ቫይረስ ክፉኛ ከተጠቁት አንዷ ስትሆን በርካታ ሞቶችም ተመዝግቧል።

የጤና ባለሙያዎች እንደሚናገሩት በህክምና ቁሳቁሶች እጥረትና እርዳታ ባለማግኘት በርካታ ሰዎች ሊሞቱ እንደሚችሉም አስጠንቅቀዋል።

የብራዚል ጤና ኃላፊዎች በመጪው እሁድም አገሪቱ ለሁለቱ ክትባቶች ፈቃድ ትስጥ በሚለው ጉዳይ ላይ ውሳኔ ያሳልፋሉ።

አንደኛው ክትባት በኦክስፎርድ ዩኒቨርስቲና በአስትራ ዜንካ የበለፀገው ሲሆን ሌላኛው ደግሞ ለድንገተኛ ጊዜ የሚውለው የቻይናው ሲኖቫክ ነው። ክትባቶቹ ፈቃድ ካገኙም ከሶስት አስከ አምስት ቀናት ባሉት ወቅት መሰጠት እንደሚጀምሩም የጤና ባለሙያዎቹ አሳውቀዋል።