ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የመን ጦርነት፡ አሜሪካ የሁቲ አማጺያንን በአሸባሪነት ልትፈርጅ ነው
አሜሪካ የየመን ሁቲ አማጺያንን እንቅስቃሴ በሽብር ቡድን ለመፈረጅ ማቀዷን አስታወቀች። ይሁን እንጂ ይህ እርምጃ በጦርነት በተጎዳችው አገር የሚካሄዱ የእርዳታ ሥራዎችን አደጋ ላይ ይጥላል የሚል ማስጠንቀቂያ እየተሰጠ ነው።
የአገሪቷ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማይክ ፖምፒዮ የዚህ ውሳኔ ዓላማ አማጺያኑ በንፁሃን ዜጎች ላይ፣ በመሰረት ልማትና በንግድ መርከቦች ላይ በሚያደርሱት ድንበር ተሻጋሪ ጥቃቶች ተጠያቂ ለማድረግ እንደሆነ ተናግረዋል።
ከዚህም በተጨማሪ በኢራን ደጋፊነት ከሚፈጽሙት "ሰይጣናዊ ተግባር" ያግዳቸዋል ብለዋል።
ይሁን እንጅ የእርዳታ ድርጅቶች ይህ መሆኑ ሚሊየኖች በረሃብ አፋፍ ላይ ባሉበት አካባቢ ከሚሰሩት የሰብዓዊ እርዳታ ሊያግዳቸው እንደሚችል ተናግረዋል።
የተባበሩት መንግሥታት ቃል አቀባይ፤ የአሜሪካ ውሳኔ ከባድ ሰብዓዊ እና ፖለቲካዊ ውጤቶችን ሊያስከትል እንደሚችል ተናግረዋል።
የዓለም አቀፉ ሬስኪዩ ኮሚቴ በበኩሉ ውሳኔውን "ግልፅ የሆነ ዲፕሎማሲያዊ ጥፋት" ብለውታል።
የሁቲ መሪ የፕሬዚደንት ዶናልድ ትራምፕን አስተዳደር በሽብርተኝነት የከሰሱ ሲሆን፤ እንቅስቃሴው ለሚሰጠው ማንኛውም ፍረጃ መልስ የመስጠት መብቱ የተጠበቀ ነው ብለዋል።
የመን እአአ 2015 የሁቲ አማጺያን የአገሪቷን ምዕራባዊ ክፍል ሲቆጣጠሩ እና በሳዑዲ የሚመራው የአረብ አገራት ጥምረት የፕሬዚደንት አብድራቡህ ማንሱር ሃዲን አገዛዝ ለመመለስ የጦር ዘመቻ ሲያካሂዱ በተቀጣጠለው ግጭት ክፉኛ ወድማለች።
ጥምረቱ ከአሜሪካ፣ ዩናይትድ ኪንግደምና ፈረንሳይ የሎጂስቲክና የደህንነት ድጋፍ ተቀብሏል።
በሌላ በኩል ኢራን ለሁቲ ሚሳይል፣ ሰው አልባ አውሮፕላኖች [ድሮን] እና ስልጠናዎችን ሰጥታለች በሚል የቀረበባትን ክስ ተቃውማለች።
በዚህ ግጭት ከ110 ሺህ በላይ ሰዎች መሞታቸው የተነገረ ሲሆን የተባበሩት መንግሥታት 'የዓለማችን አስከፊው ሰብዓዊ ቀውስ' ላለው ችግር ተዳርጋለች። 80 በመቶ የሚሆነው ሕዝቧም ድጋፍ ወይም ጥበቃን ይሻሉ።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ፖምፒዮ እሁድ እለት፤ መሥሪያ ቤታቸው ፕሬዚደንት ትራምፕ ዋይት ሃውስን ለቀው ከመውጣታቸው አንድ ቀን በፊት 'አንሳር አላህ' [የፈጣሪ ወገን] በመባል የሚታወቀውን የሁቲ አማጽያን፤ በውጭ የሽብር ድርጅት ለመፈረጅ ያለውን ዓላማ ለኮንግረሱ እንደሚያቀርቡ ተናግረዋል።
በዚህም መሠረት ሦስት የሁቲ መሪዎች፤ አብዱል ማሊክ አል-ሁቲ፣ አብዱል ሃሊቅ ባደር አል-ዲን አል-ሁቲ እና አብዱላህ ያህያ አል-ሃኪም በዓለም በልዩ ሁኔታ የተፈረጁ አሸባሪዎች ዝርዝር ውስጥ ይገባሉ።
ቡድኑ በሽብር መፈረጁ ሰላማዊ፣ ሉዓላዊ እና ከኢራን ጣልቃ ገብነት የፀዳች እና ከጎረቤቶቿ ጋር ሰላም የሆነች አንድነቷ የተጠበቀ የመንን ለመፍጠር ጥረት ለማድረግ የታቀደ እንደሆነ ፖምፒዮ ተናግረዋል።
ውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ "ጭካኔ የተሞላበት ጥቃት" ያሉትና 27 ሰዎችን የገደለው በደቡባዊ ከተማዋ አደን አየር ማረፊያ ታኅሳስ ሰላሳ የተፈፀመውን ጥቃት አንስተዋል።
በሳዑዲ የሚደገፈው የየመን መንግሥት ይህንን ጥቃት ከሁቲዎች ጋር ያገናኙት ቢሆንም፤ ሁቲዎች ግን የቀረበባቸውን ውንጃላ ተቃውመውታል።
የሁቲ መሪ ሞሃመድ አሊ አል-ሁቲ ሰኞ ዕለት በትዊተር ገጻቸው ባሰፈሩት ጽሁፍ "አሜሪካ የሽብር ምንጭ ናት፤ የትራምፕ አስተዳደር ፖሊሲና ድርጊቱ አሸባሪ ነው፤ ለየመን ሕዝብ ግድያና ረሃብ ተባባሪ ስለሆነ ለየመን ግድ የለውም" ብለዋል።
አክለውም አማጺያኑ " በትራምፕ አስተዳደር ሆነ በሌላ አስተዳደር ለሚመጣበት ፍረጃ መልስ የመስጠት መብቱ የተጠበቀ ነው" ሲሉ አቋማቸውን ገልፀዋል።
የየመን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በበኩሉ የአሜሪካን እርምጃ እንደሚደግፍና በሁቲዎች ላይ ተጨማሪ ፖለቲካዊና ሕጋዊ ጫናዎች እንዲደረጉ ጥሪ ማቅረቡን ሮይተርስ የዜና ወኪል ዘግቧል።