ኮሮናቫይረስ ፡ በዩናይትድ ኪንግደም ከ80 ሺህ በላይ ሰዎች በኮቪድ-19 መሞታቸው ተገለጸ

የፎቶው ባለመብት, PA Media
የኮሮናቫይረስ ከተከሰተ በአንድ ዓመት ውስጥ በዩናይትድ ኪንግደም ከ80 ሺህ በላይ ሰዎች በወረርሽኙ ምክንያት መሞታቸው ይፋ ሆኗል።
ትናት ቅዳሜ በዩናይትድ ኪንግደም ተጨማሪ በበሽታው ሳበያ የ1 ሺህ 35 ሰዎች ሞት ሪፖርት የተደረገ ሲሆን፤ ይህም አጠቃላይ የሟቾችን ቁጥር ወደ 80 ሺህ 868 ከፍ አድርጎታል። በየቀኑ በኮሮናቫይረስ የሚያዙ ሰዎች ቁጥርም በ59 ሺህ 937 ጨምሯል።
የጆንስ ሆፕኪንስ ዩኒቨርሲቲ መረጃ እንደሚያሳየው ከሆነ በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ከፍተኛ ሞት ያስመዘገቡ አገራት አሜሪካ፣ ብራዚል፣ ሕንድ እና ሜክሲኮ ናቸው።
አሁን ቫይረሱ አሳሳቢ ደረጃ ላይ የደረሰባት ዩናይትድ ኪንግደም ደግሞ በተከታታይ ከ1 ሺህ በላይ የኮሮናቫይረስ ታማሚዎች ሞት ስታስተናግድ አራተኛ ቀኗን አስቆጥራለች። ይህም የሆነው መንግሥት እንግሊዝን ዝግ ሙሉ በሙሉ እንዲያደርግ ሳይንቲስቶች ሃሳብ ባቀረቡበት ጊዜ ነው።
በባለሥልጣናት ዜጎች ቫይረሱ እንዳለባቸው አስበው እንዲንቀሳቀሱ መክረዋል። ባለፈው ቅዳሜም የ94 ዓመቷ የእንግሊዝ ንግሥት እና የ99 ዓመቱ የኤዲንብራው መስፍን የኮቪድ-19 ክትባት መውሰዳቸውን የባኪንግሃም ቤተመንግሥት ይፋ አድርጓል።
የእንግሊዝ የብሔራዊ ስታቲስቲክስ መሥሪያ ቤት መረጃ እንደሚያሳየው ከፈረንጆቹ ታኅሣስ 27 እስከ ጥር 2 ባለው ጊዜ ውስጥ ብቻ በእንግሊዝ ከ50 ሰዎች መካከል ቢያንስ አንዱ የኮሮናቫይረስ አለበት። በለንደን ከተማ ብቻ ሲታይ ደግሞ ከ30 ሰዎች አንዱ ቫይረሱ እንዳለበት ያሳያል።
የእንግሊዝ የኅብረተሰብ ጤና መረጃ እንደሚያሳየው ከሆነ በአካባቢ ሲታይ ከ100 ሺህ ሰዎች መካከል ከ1 ሺህ በላይ ሰዎች በቫይረሱ በመያዝ የለንደን ከተማ በዩናይትድ ኪንግደም ከፍተኛው ነው። በመላው አገሪቱ በተጣለው የእንቅስቃሴ ገደብ ምክንያት ሰዎች በእንግሊዝ ለወሳኝ ጉዳይ ካልሆነ ከቤት እንዳይወጡ ተደርጓል።
ስኮትላንድ፣ ዌልስና ሰሜን አየርላንድም በብዙ አካባቢዎቻቸው ላይ ተመሳሳይ እገዳ ጥለዋል።
ፕሮፌሰር ሮበርት ዌስት የተባሉ ምሁር ቫይረሱ ባለፈው ዓመት መጋቢት ላይ ከነበረበት ሁኔታ ጋር ሲነጻጸር የአሁኑ ቢያንስ በ50 በመቶ የመስፋፋት እድሉን የጨመረ መሆኑን ተናግረዋል።
በአሁኑ ወቅት ትምህርት ቤቶች ተከፍተዋል። ብዙ ሕጻናትም ወደ ትምህርት ቤት እየሄዱ ነው። በመሆኑም ቫይረሱ በኅብረተሰቡ ውስጥ እንዲስፋፋ ትምህርት ቤቶች ከፍተኛ ሚና ይጫወታሉ ብለዋል።
ሳይንቲስቶች ደግሞ የአሁኑ የቫይረሱ ስርጭት ባለፈው ከነበረበት ሁኔታ ጋር ሲነጻጸር ከ50 እስከ 70 በመቶ ሊጨምር እንደሚችል ይገምታሉ።
የለንደን አካባቢ የኅብረተሰብ ጤና ዳይሬክተር የሆኑት ፕሮፌሰር ኬቪን ፌንቶን "ብዙ ልናከናውናቸው የሚገቡ ነገሮች ነበሩ" ብለዋል የሕዝቡ ጭምብል አለማድረግና አካላዊ ርቀት ያለመጠበቅ ሁኔታ በመተቸት።












