አሜሪካ የሰሜን ኮሪያ 'ትልቋ ጠላት' ናት - ኪም ጆንግ ኡን

ታትሟል

አሜሪካ የአገራቸው "ትልቋ ጠላት" መሆኗን የሰሜን ኮሪያው መሪ ኪም ጆንግ-ኡን በመግለጽ በነጩ ቤተመንግሥት ማንም ፕሬዝዳንት ቢሆን ፒዮንግያንግን በተመለከተ ዋሽንግተን ፖሊሲዋን ትቀይራለች ብለው እንደማይጠብቁ ገለጹ።

ኪም በገዢው የሠራተኛ ፓርቲ ብዙም ያልተለመደ ስብሰባ ላይ ንግግር ሲያደርጉ የሰሜን ኮሪያን የኒውክሌር የጦር መሣሪያና የጦር አቅም እንደሚያሳድጉ ቃል ገብተዋል።

የኒውክሌር ሰርጓጅ መርከብ ዕቅድ ለመጠናቀቅ ጫፍ ደርሷል ብለዋል።

ኪም ይህንን የተናገሩት የአሜሪካው ተመራጭ ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ስልጣናቸውን ለመቀበል በዝግጅት ላይ ባሉበት ወቅት ነው።

ተንታኞች እንደሚሉት ኪም አስተያየት የሰጡት ባይደን በቅርቡ ቃለ መሃላ በመፈጸም በሚመሠርቱት በአዲሱ የአሜሪካ አስተዳደር ላይ ጫና ለማሳደር የሚደረግ ጥረት ነው።

በሰሜን ኮሪያ የኒውክሌር መርሃ ግብር ዙሪያ በተደረጉ ውይይቶች ብዙም ተጨባጭ ውጤት ባይመጣም ኪም ከተሰናባቹ የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ጋር ሞቅ ያለ ወዳጅነት ነበራቸው።

ለሠራተኞች ፓርቲው በታሪኩ ስምንተኛ በሆነው ስብሰባ ባደረጉት ንግግር ኪም ፒዮንግያንግ "የጠላት ኃይሎች" ቀድመው በአገራቸው ላይ ጥቃት ሊሰነዝሩ ካላሰቡ ፒዮንግያንግ የኒውክሌር መሣሪያዎቿን ለመጠቀም አታስበም ብለዋል።

"አሜሪካ ለአገራቸን አብዮት ታላቋ ጠላታችን እና ትልቋ መሰናክል ነች ... ማንም ስልጣን ቢይዝ በሰሜን ኮሪያ ላይ ያለው የፖሊሲው አይቀየርም" ማለታቸውን የአገሪቱ መንግሥት ዜና ወኪል ዘግቧል።

በንግግራቸውም ከመሬት ወይም ከባሕር መወንጨፍ የሚችሉ ረዥም ርቀት ባላስቲክ ሚሳኤሎችን ጨምሮ የጦር መሣሪያዎቻቸውን ዝርዝር ይፋ አድርገዋል።

ሰሜን ኮሪያ ጥብቅ የኢኮኖሚ ማዕቀብ ቢጣልባትም የጦር መሣሪያ ግንባታ ፕሮግራሟን በከፍተኛ ደረጃ ለማሳደግ ችላለች።

ኪም በዚህ ሳምንት መጀመሪያ ተገልላ ለምትገኘው አገራቸው የጸደቀው የአምስት ዓመት የኢኮኖሚ ዕቅድ "በሁሉም ዘርፍ ማለት በሚቻል መልኩ" ማሳካት አለመቻሉን አምነዋል።

ሰሜን ኮሪያ የኮሮናቫይረስ በአገሪቱ አለመመዝገቡን ብትገልጽም ስርጭቱን ለመከላከል ጥቅምት ድንበሮቿን ዘግታለች።

ከጎረቤቷ እና አጋሯ ቻይና ጋር የነበራት ንግድ ልውውጥ በ80 በመቶ ገደማ ወርዷል። አውሎ ነፋሶችና ጎርፍ የኒውክሌር ፕሮግራሙን ጨምሮ በጥብቅ ዓለም አቀፍ ማዕቀቦች ውስጥ በምትገኘው ሰሜን ኮሪያ ቤቶችን እና ሰብሎችን አውድሟል።