ኮሮናቫይረስ ፡ የሞደርና ክትባት በዩናይትድ ኪንግደም ፈቃድ በማግኘት ሦስተኛው ሆነ

ክትባት

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ታትሟል

ሦስተኛው የኮቪድ-19 ክትባት በዩናይትድ ኪንግደም ውስጥ እንዲሰጥ ፈቃድ አገኘ።

ክትባቱ በአሜሪካ ኩባንያ ሞደርና የተሠራ ሲሆን ከፋይዘር ጋር ተመሳሳይ በሆነ መንገድ ይሠራል ተብሏል።

ዩናይትድ ኪንግደም 10 ሚሊዮን ክትባቶችን ያዘዘች ሲሆን፤ አጠቃላይ ትዕዛዙ ወደ 17 ሚሊዮን ቢደርሰም አቅርቦቱ ግን ጊዜ እንደሚፈልግ ተነግሯል።

እንግሊዝ ውስጥ 1.5 ሚሊዮን ያህል ሰዎች እስካሁን ድረስ ቢያንስ አንድ ጊዜ የኮቪድ-19 ክትባት ወስደዋል። አንዳንድ ክትባቶች ከመጀመሪያ ክትባት ጥቂት ሳምንታት በኋላ ለሁለተኛ ጊዜ መከተብን ስለሚጠይቁ ሌላ ዙር ክትባት አስፈላጊ ነው።

ይህ አሃዝም ከ80 ዓመት በላይ ከሆኑት መካከል አንድ አራተኛ የሚሆኑትን ያካትታል ተብሏል።

በእንግሊዝ ውስጥ ወደ 30 ሚሊዮን የሚጠጉ ሰዎችን የሚሸፍን ዘጠኝ ከፍተኛ ቅድሚያ በሚሰጣቸው ምድብ ዝርዝር ውስጥ እንደተጠቀሰው፤ ክትባቶቹ በመጀመሪያ ደረጃ በጣም ተጋላጭ ለሆኑት እየተሰጡ ናቸው።

ጠቅላይ ሚኒስትር ቦሪስ ጆንሰን እንዳሉት፤ ዓላማው በእንግሊዝ ውስጥ እስከ የካቲት አጋማሽ ድረስ 15 ሚሊዮን ሰዎችን መክተብ ነው።

የጤናና ማኅበራዊ እንክብካቤ ሚንስትሩ ማት ሀንኮክ "ዜናው ይህን አስከፊ በሽታ ለመግታት ሌላ መሣሪያ ነው" ብለዋል።

እንግሊዝ በመጀመሪያ 7 ሚሊዮን ክትባቶችን ያዘዘች ቢሆንም ብዙ ሰዎችን እንዲከተቡ ለማድረግ ቁጥሩን ወደ በ10 ሚሊዮን አድርጓል።

በአጠቃላይ እንግሊዝ ኮቪድ -19ን ለመከላከል 367 ሚሊዮን የክትባት ብልቃጦችን አዛለች።

የሞደርና ክትባት ከተለመደው ማቀዝቀዣ ጋር የሚመሳሰልና ለማጓጓዝ ከዜሮ በታች 20 ሴልሺየስ አካባቢ ያህል የቅዝቃዜ መጠን ይፈልጋል።

ለንጽጽር ያህል የፋይዘር/ባዮንቴክ ክትባትን ለማጓጓዝ ከዜሮ በታች ወደ 75 ሴሊሼስ የሚጠጋ የቅዝቃዜ መጠን የሚፈለግ ሲሆን፤ ይህም የትራንስፖርት አቅርቦት ሁኔታን በጣም ከባድ ያደርገዋል ተብሏል።

የአስትራዜኔካ ክትባት በተለመደው የማቀዝቀዣ ሙቀት ሊቆይ ስለሚችል ለማከማቸት እና ለማሰራጨት ቀላል እንደሆነ ተነግሯል።

ሁሉም ክትባቶች ለሁለተኛ ጊዜ የማጠናከሪያ ክትባት የሚፈልጉ ሲሆን የመጀመሪያ ዙርን በተቻለ መጠን ለብዙ ሰዎች ሊሰጥ ይችላል።

ከ30 ሺህ በላይ በሆኑ ሰዎች ላይ በተደረገ ሙከራ የሞደርና ክትባት ወደ 95% የሚጠጉትን ሰዎች ከኮቪድ-19 መከላከል ችሏል።

የትኛውም ክትባት 100 በመቶ ውጤታማ አልሆነም። እዚህ ላይ ለመድረስ ጊዜ ይወስዳል። ሁሉም የኮቪድ-19 ክትባቶች የበሽታ መከላከያ አቅምን ፈጥረው ለምን ያህል ጊዜ እንደሚቆይ አይታወቅም።

የኮሮቫይረስ ክትባት የወሰዱ ሰዎች እራሳቸውን እና ሌሎችን ለመጠበቅ ማኅበራዊ ርቀትን የሚመለከቱ ሕጎችን መከተል መቀጠል አለባቸው ተብሏል።

የአውሮፓ ሕብረት ተቆጣጣሪዎች የሞደርና ክትባት ቀደም ብለው ማጽደቃቸው ይታወሳል።