ደቡብ ኮሪያ በኢራን የተያዘባት ኬሚካል የጫነ መርከብ እንዲለቀቅ ጠየቀች

የደቡብ ኮሪያን ባንዲራ የሚያውለበልበው እቃ ጫኝ መርከብ የተያዘው በኢራን ወታደሮች ነው

የፎቶው ባለመብት, EPA/TASNIM NEWS AGENCY

ታትሟል

ደቡብ ኮሪያ በኢራን የተያዘባት የኬሚካል የጫነ መርከብ እንዲለቀቅ ጥረት እያደረገች ነው።

ኤምቲ ሃንኩክ ቼሚ በሆርሙዝ ስትራቴጂካዊ የባሕር ዳርቻ አቅራቢያ በኢራን ኃይሎች የተያዘ ሲሆን 20 ሠራተኞቹም ታስረዋል።

ኢራን መርከቡ የአካባቢ ጥበቃ ደንቦችን ጥሷል ብላለች፡፡

ድርጊቱ የተከሰተው በአሜሪካ ማዕቀብ ምክንያት በደቡብ ኮሪያ ባንኮች ውስጥ የሚገኘው የኢራን ገንዘብ ላይ እገዳ መጣሉን ተከለትሎ ነው፡፡

በጉዳዩ ላይ ለመወያየት አንድ የደቡብ ኮሪያ ከፍተኛ ባለስልጣን ልዑክ በሚቀጥሉት ቀናት ወደ ኢራን ያቀናል ተብሏል።

አንድ ባለሥልጣን የምክትል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቾይ ጆንግ-ኩን ጉብኝት ስለመካሄዱ አለመካሄዱ "እቅዱ ግልጽ አይደለም" ሲሉ ለሮይተርስ የዜና ወኪል ተናግረዋል፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ካንግ ክዩንግ-ወሃ ለጋዜጠኞች እንደገለጹት፣ ደቡብ ኮሪያ ታንከሩ እና ሠራተኞቹ እንዲለቀቁ ዲፕሎማስያዊ ጥረት እያደረገች ነው።

ሠራተኞቹ የተለያዩ አገራት ዜግነት ያላቸው ናቸው የተባለ ሲሆን ከኢንዶኔዥያ፣ ከማይናማር፣ ከደቡብ ኮሪያ እና ከቬትናም የመጡ መርከበኞችን ያካተተ መሆኑ ተነግሯል።

"በደቡብ ኮሪያ የኢራን ኤምባሲ እና በኢራን የደቡብ ኮሪያ ኤምባሲ በኩል የተከሰተውን ለማጣራት ጥረት እያደረግን ሲሆን ሁኔታው ለመቅረፍ እየሞከርን ነው" ሲሉ መግለጻቸውን የዮናፕ የዜና ወኪል ዘግቧል፡፡

የደቡብ ኮሪያ የመከላከያ ሚኒስቴር የደቡብ ኮሪያ ዜጎችን "ደህንነት ለማረጋገጥ" አንድ ቡድን ወደ ባህረ ሰላጤው አካባቢ መላኩን አስታውቋል፡፡

የኢራን የውጭ ጉዳይ ሚንስትር ቃል አቀባይ በሰጡት መግለጫ የኬሚካል ታንከሩ የተያዘው "በቴክኒካዊ ጉዳይ እና ባህሩን በመበከሉ ምክንያት ብቻ ነው" ብለዋል፡፡

የመርከቡ ተቆጣጣሪ ግን መርከቡ ውሃውን እየበከለ ነው መባሉን አስተባብሏል፡፡

ክስተቱ ኢራን ከአንድ አመት በሚበልጥ ጊዜ ውስጥ አንድ ትልቅ መርከብ ስትይዝ የመጀመሪያው አድርጎታል፡፡