በኮሮናቫይረስ ወቅት በአውሮፕላን አደጋ የተከሰተ ሞት ጨምሯል ተባለ

ታትሟል

ባለፈው ዓመት በቻይና ተከስቶ መላው ዓለምን ያዳረሰው የኮሮናቫይረስ ክፉኛ ከጎዳቸው ዘርፎች መካከል የአውሮፕላን ትራንስፖርት አንዱ ነው።

በብዙ አገራት የበረራ ገደብ በመጣሉ የአውሮፕላን ጉዞ በእጅጉ ተዳክሞ ቆይቷል። የበረራው ቁጥር መቀነስ ግን በዘርፉ የሚደርሰውን የሞት አደጋ አልቀነሰውም።

አንድ የዘርፉ ተቋም እንዳለው በፈረንጆቹ 2020 በኮሮናቫይረስ ሳቢያ የአውሮፕላን በረራዎች ቢቀንሱም በንግድ አውሮፕላኖች መከስከስ ምክንያት የሞቱ ሰዎች ቁጥር ግን ከወትሮው በተለየ ሁኔታ አሻቅቧል።

'ቱ70' የተባለው የኔዘርላንድስ የበራራ አማካሪ ድርጅት ባወጣው መረጃ መሰረት ባለፈውረ ዓመት በመላው ዓለም በንግድ አውሮፕላኖች መከስከስ ምክንያት 299 ሰዎች ሕይወታቸውን አጥተዋል።

ይህም በ2019 ከነበረው 257 የሞት አደጋ ጋር ሲነጻጸር በ42 ብልጫ አለው። ይህ የሆነው ደግሞ የአውሮፕላን በረራ በከፍተኛ ሁኔታ ገደብ ተጥሎበት በነበረበት የፈረንጆቹ 2020 ነው።

በረራዎችን የሚከታተለው 'ፍላይትራዳር 24' የተባለው ተቋም ባወጣው መረጃ መሰረት ደግሞ ባለፈው የፈረንጆቹ ዓመት የንግድ አውሮፕላን በረራዎች የኮሮናቫይረስን መከሰት ተከትሎ በተጣለው ገደብ ምክንያት በ42 በመቶ እንቅስቃሴያቸው ቀንሶ ነበር።

በቱ70 ሪፖርት እንደተካተተው ከትልልቅ የመጓጓዣ አውሮፕላኖች አደጋ ጀምሮ በመሣሪያ ተመትተው እስከ ወደቁ አውሮፕላኖች ድረስ ያለውን የአደጋ ሁኔታ በሪፖርቱ አካትቷል። ሪፖርታቸው ባለፈው ዓመት ጥር ወር ላይ በኢራን የተመታውን የዩክሬን ዓለም አቀፍ በረራንም አካቷል።

የዩክሬኑን የአውሮፕላን ላይ ኢራን በሰነዘረችውን ጥቃት ተከትሎ በአውሮፕላኑ ውስጥ ከነበሩት ተሳፋሪዎች መካከል 179 ሰዎች ሞተዋል። ለእነዚህ ሟች ቤተሰቦችም ለእያንዳንዳቸው 150 ሺህ የአሜሪካን ዶላር ካሳ ለመስጠተት ኢራን ተስማምታለች።

በግንቦት ወር ካራቺ በተባለች ከተማ ውስጥ ተከስክሶ 98 ሰዎችን የገደለው የፓኪስታን ዓለም አቀፍ አየር መንገድ በረራንም ሪፖርቱ አካቷል። ይፋ በሆነው ጊዜያዊ ሪፖርት መሰረት የእዚህ አውሮፕላን የአደጋው ምክንያት "የሰው ስህተት" ነው ተብሏል።

በሌላ በኩል የሟቾች ቁጥር መጨመሩ እንዳለ ሆኖ የደረሰው የአደጋ መጠን ግን በ2019 ከነበሩት 86 አደጋዎች ጋር ሲነጻጸር ወደ 40 ዝቅ ማለቱን ቱ70 በሪፖርቱ ገልጿል።

ከእነዚህ 40 አደጋዎች መካከል አምስቱ ብቻ ከባድ ጉዳትን ያስከተሉ እንደነበሩም ታውቋል። ነገር ግን የበረራ አማካሪ ድርጅቱ እንደሚለው ከሆነ እንዲህ አይነቱ ካለፉት 10 ዓመታት አማካይ ጋር ተመሳሳይነት አለው።

በመሆኑም የበረራ መቀነስ በአብራሪዎች ተግባር ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ አሳድሯል፤ በዚህ ምክንያትም ወደ መደበኛ በረራ ሲገባ የክህሎት መቀነስ ለኢንዱስትሪው ወሳኝ ክፍተት ይሆናል ብሏል።

በዓለም አቀፍ በረራ በሰላማዊነቱ በክብረወሰንነት የተመዘገበው 2017 ዓመት ነው። በ2017 ምንም አደገኛ የአውሮፕላን አደጋ አልተስተናገደም። ሁለት አካባቢያዊ በረራዎች [ልምምድ] ላይ በደረሰ አደጋ ብቻ 13 ሰዎች ሞተዋል።