በዩክሬን አውሮፕላን ተከስክሶ 22 ሰዎች ሞቱ

ታትሟል

በዩክሬን ባጋጠመ የአውሮፕላን የመከስከስ አደጋ ቢያንስ 22 ሰዎች መሞታቸው ተገለጸ።

ከሟቾቹ መካከል አብዛኛዎቹ ሰልጣኝ አብራሪዎች መሆናቸውን የዩክሬን ባለስልጣናት አስታውቀዋል።

ሩስያ ሰራሹ አንቶኖቭ-26 አውሮፕላን የተከሰከሰው በምስራቃዊ ዩክሬን ከተማ ለማረፍ በተቃረበበት ወቅት ነበር።

አውሮፕላኑ ከአገሪቱ አየር ኃይል አየር ማረፊያ መነሳቱ እና የልምምድ በረራ እንደነበረ ተነግሯል።

የዩክሬን የአደጋ ጊዜ ሚንስቴር እንዳለው 27 ሰዎች በአውሮፕላኑ ተሳፍረው ነበር። 22ቱ መሞታቸው ሲረጋገጥ ሁለት ሰዎች ከፍተኛ ጉዳት ደርሶባቸው ህክምና ላይ ይገኛሉ። ቀሪ ሶስት ሰዎች ደግሞ እየተፈለጉ ነው።

የአደጋው ምክንያት በመጣራት ላይ ይገኛል ተብሏል።

አደጋው የደረሰው አፍቃሪ ሩሲያ ከሆኑት ተገንጣይ ኃይሎች ድንበር በ100 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ነው።

ይሁን እንጂ አደጋው በዩክሬን ካለው ግጭት ጋር የሚያገናኘው ነገር የለም ብለዋል የአገሪቱ ባለስልጣናት።

አደጋው እንደደረሰ አውሮፕላኑ በእሳት ተያይዞ እንደነበረ ተነግሯል። አንድ የዓይን እማኝ በእሳት እየተቃጠለ ሲሮጥ የነበረ ሰው ተመልክቻለሁ ሲል ለሬውተርስ ተናግሯል።

ፕሬዝደንት ቮሎደይመይር ዜሌኒስኪ አደጋው ወደደረሰበት ስፍራ ይጓዛሉ ተብሏል።