ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ተዋናይ፣ ደራሲና አዘጋጅ ባዩሽ ዓለማየሁ
ተዋናይት፣ ደራሲ እና አዘጋጅ ባዩሽ ዓለማየው ታኅሣስ 23 ቀን 2013 ዓ. ም. ከዚህ ዓለም በሞት ተለይታለች።
በተለይም በአገር ፍቅር ቴአትር ቤት ለበርካታ ዓመታት በተውኔት ሥራዎቿ የምትታወቀው ባዩሽ የመድረክ ቴአትር አዘጋጅም ነበረች።
ባዩሽ ከምትታወቅባቸው ሥራዎች መካከል "ነቃሽ" የተባለው ቴአትር ይጠቀሳል።
በአዲስ አበባ ማዘጋጃ ቤት የባህልና ቴአትር አዳራሽ የቀረበው ይህ ቴአትር የሕክምና ተቋማት ውስጥ ስለሚከሰቱ ሴራዎች ይተርካል።
የአስክሬን ዘረፋ፣ የመድኃኒት ሽያጭና ሌሎችም ቴአትሩ የሚያጠነጥንባቸው ርዕሰ ጉዳዮች የተመልካችን ቀልብ ስበው ነበር።
ከባዩሽ በተጨማሪ ፋንቱ ማንዶዬና ሌሎችም አንጋፋ ተዋንያንን ያሳተፈው ቴአትሩ ከ28 ዓመታት በኋላ በድጋሚ ወደ መድረክ እንዲመለስ መደረጉም ይታወሳል።
ባዩሽ አጫጭር ተከታታይ ድራማዎችና ትረካዎችም ሠርታለች።
ከሥራዎቿ መካከል ነቃሽ፣ ትዳር ሲታጠን፣ የስለት ልጅ፣ ሰማያዊ ዐይን፣ የቬኑሱ ነጋዴ እና ሰዓት እላፊ ተጠቃሽ ናቸው።
የታዋቂው ተርጓሚ እንዲሁም ደራሲ መስፍን ዓለማየሁ ልጅ የሆነችው ባዩሽ በሬድዮ ትረካም ትታወቃለች።
በዚህም በሬድዮ ፋና ላይ "ፓፒዮ" የተሰኘውን ትርጉም ልብ ወለድን መተረኳ ይታወሳል።
በ1990ዎቹ ገደማ በኢትዮጲያ ቴሌቪዥን ስመ ገናና በነበሩ አጫጭር ተከታታይ ድራማዎች ላይ በመተወን የታወቀችው ባዩሽ፤ ከድርሰት ሥራዎቿ ውስጥ ረመጥ፣ ፎርፌ እና ገጽ ሁለት ተጠቃስ ናቸው።
ተዋናይ፣ ደራሲና አዘጋጅ ባዩሽ ታማ ሆስፒታል እስከምትገባ ድረስ በአገር ፍቅር ቴአትር ቤት በድጋሚ ሊታይ በነበረው "ሰዓት እላፊ" በተሰኘው የቴዎድሮስ ተክለአረጋይ ቴአትር ላይ ለመተወን በልምምድ ላይ እንደነበረች ተነግሯል።
ባጋጠማት ህመም ምክንያት በየካቲት 12 ሆስፒታል በህክምና ስትረዳ ቆይታ ታህሳስ 23 ቀን 2013 ዓ. ም 11 ሰዓት ገደማ ከዚህ ዓለም በሞት መለየቷን ቤተሰቦቿ ገልጸዋል።
ስለባዩሽ የሚያውቋት በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ያሉት
መዓዛ ወርቁ
መድረክ ላይ የምደነቅባት ተዋናይት (ሥራዎቿን ዘርዝሬ አልጨርሳቸውም። ገብቷት ተመችቷት የምትኖርበት መድረክ።)
በሥራዎቼ የማምናት የእኔ የምላት ተዋናይት፤ አቋራጩ - የቲቪ፣ ወፌ ቆመች እና ህይወት መሰናዶ የሬዲዮ ድራማዎች ላይ አፌን ያስከፈተችኝ ሙሉ ሴት።
አገር ፍቅር ቲያትር ቤት የሴት ደራሲ ነበረኝ ካለ ከባዩሽ ሌላ ማንን እንደሚጠራ አላውቅም።
ቆንጆ ቆንጆ አጫጭር ልቦለድ ፅሁፎቿን ለሬዲዮ ራሷ ተርካ ሰጥታናለች - ታሪክ የገባት ሀሳብ ያላት ደራሲ!
አደንቃታለሁ አከብራታለሁ እወዳታለሁ። በህልፈቷ እጅግ አዝኛለሁ።
እኔ በህይወት እስካለሁ አልረሳትም። ታሪኳ በኢትዮጵያ ኪነጥበብ ታሪክ ጥሩ ቦታ እንዲቀመጥ እመኛለሁ።
**
ያሬድ ሹመቴ
ከድንቅ ተዋናይነቷ በላይ ፊቴ ድቅን የሚለው በጎነቷ ነው። በአገር ፍቅር ቴአትር ቤት እንደመስራቷ የእርዳታ ማስተባበር ሥራዎች በምንሰራባቸው ጊዜያት እህል ጭኖ ለማራገፍ የቆመ መኪና ስታይ ድንገት ነገሯን ሁሉ ትታ ወደ ሸክም እርዳታ ትገባለች።
ከያኒ ባዩሽ አለማየሁ ገና ብዙ በምትሰራበት እድሜዋ አጥተናታል። እንግዲህስ ምን እንላለን? ቸር አምላክ ከደጋጎቹ ወገን ያኑራት።
**
መሰረት መብራቴ
የኔ ምስኪን በመጨረሻም ወደማይቀረው ቤትሽ ሄድሽ።
ባዩሽ አለማየሁ ፀሐፌ ተውኔት፣ አዘጋጅ፣ ምርጥ ተዋናይት! የብርቱና የጠንካሬ ሴት ተምሳሌት!
አይጠገቤ ጨዋታሽ፣ አክብሮትሽ እና መልካም ሰብዕናሽ ሁሌም በልባችን ይኖራል።
**
ወሰንሰገድ ገ/ኪዳን
ባዩሽ፤ ከምርጥ ሴት ተዋናዮች ተርታ የምትጠቀስ ነበረች፤ ለመድረክ ትወና የተሰጠች የጥበብ እመቤት ነበረች፤ ድንቅ ተዋናይ ነበረች።
**
ውድነህ ክፍሌ
የኛ አንደኛ፤ መድረክን እየናፈቁ መለየት ልብ ይሰብራል። ደራሲ፣ አዘጋጅና ተዋናይት ባዩሽ አለማየሁ። ነፍስሽ በሰላም ትረፍ።