“አልማዝ በአማርኛም በእንግሊዘኛም ታስቀን ነበር” አልማዝ ኃይሌ ስትታወስ

ታትሟል

በትወና እንዲሁም በማስታወቂያም አንጋፋ ከሆኑ ባለሙያዎች ማሚ በሚለው ቅጽል ስሟ የምትታወቀው አልማዝ ኃይሌ ከዚህ ዓለም በሞት ተለየች።

ለሳምንታት ታማ የነበረችው አልማዝ ዛሬ ማለዳ እንዳረፈችና ሥርዓተ ቀብሯ ነገ በመንበረ ፀባኦት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል እንደሚፈጸም ብሔራዊ ቴሌቪዥን ጣቢያው ዘግቧል።

በቴአትር፣ በፊልም፣ በተከታታይ የቴሌቭዥን እና ሬዲዮ ድራማዎች እንዲሁም በማስታወቂያ ዘርፍም ለዓመታት የሠራችው አልማዝ ስመ ጥር ከሆኑ የኪነ ጥበብ ሰዎች አንዷ ናት።

የሙያ አጋሯን እና በማስታወቂያ ሥራ አብሯት የሰሩ ሰዎችን አነጋግረናል። በቅርብ ከሚያውቋት መካከል በጽሑፍ፣ በዝግጅት፣ በትወናና ሌሎችም የጥበብ ሙያዎች የሚታወቀው ተስፋዬ አበበን ስለ አልማዝ የሚከተለውን ብሎናል።

“በቅርቡ ባልና ሚስት ሆነን ተውነን ነበር”

ተስፋዬ አልማዝን የሚያስታውሳት ብሔራዊ ቴአትር (የቀድሞው ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ቴአትር) በተወዛዋዥነት ስትቀጠር ነው።

ከአራት ዓሠርታት በፊት ከነአልጋነሽ ታሪኩ ጋር ዘመናዊና ባህላዊ ውዝዋዜ ያቀርቡ ነበር። ከዛም ወደ ትወናው ገባች።

“አልማዝ ኮሜድያን ነች። በጣም ታስቀናለች” ሲል ተስፋዬ ያስታውሳታል።

ከብሔራዊ ቴአትር ጡረታ ከወጣች በኋላ “በፊልሙ ዘርፍ ይሻሟታል” ሲል ከሷ ጋር ለመሥራት በርካቶች እንደሚጓጉም ይናገራል።

“አልማዝ ቁምነገረኛም ናት። ለአገሯ ልዩ ፍቅር አላት” የሚለው ተስፋዬ በቅርቡ ባልና ሚስት ሆነው በተከታታይ ድራማ ላይ መተወናቸውን ነግሮናል።

ድራማው ላይ ተስፋዬ የደን ልማት ሠራተኛ ሲሆን ከባለቤቱ ጋር አዘውትርው ሲጋጩ ይታያል። ከዛም ልጆቻቸው ጣልቃ ይገቡና እርቅ ይወርዳል።

ተስፋዬ ከድራማው የማይረሳው ክፍል አልማዝ የምትጫወታት ገጸ ባህሪ መርዶ ተነግሯት ስታለቅስ ነው።

“እውነተኛ እንባ እያፈሰሰች ነበር። የማስመሰል ብቃቷ የሚገርም ነው። 'facial expression' የምንለው የተዋጣላት ናት።”

ለሻይ እረፍት ሲያደርጉ አልማዝ በጣም ታስቃቸው እንደነበርም ያስታውሳል። “በአማርኛም በእንግሊዘኛም ታስቀን ነበር” ይላል።

አልማዝ ብሔራዊ ቴአትር ሳለች ከአልጋነሽ ታሪኩ፣ አሰለፈች በቀለ፣ ጠለላ ከበደ፣ አስናቀች ወርቁና ከሌሎችም በርካታ እውቅ ባለሙያዎች ጋር ሠርታለች።

በአንድ ቴአትር መነኩሴ ሆና የተወነችውን ተስፋዬ አይረሳውም። አልማዝ “ትራጀዲም ኮሜዲም ይዋጣላታል” የሚለውም ለዚህ ነው።

በማስታወቂያው ዘርፍ የሸኖ ለጋ ቂቤ ማስታወቂያን በርካቶች አይዘነጉትም።

ተስፋዬም “ሸኖ ለጋ ቂቤን ያስተዋወቀችው ግሩም አርጋ ነው። ምስሏ በየቢልቦርዱ ተሰቅሎ እንደነበር ትዝ ይለኛል” ይላል።

አልማዝ ያልተጫወተችው አይነት ገጸ ባህሪ አለ ለማለት ይከብዳል።

ተስፋዬ የሚገልጻትም “ትወና የተፈጥሮ ጸጋዋ ነው። ማንም ሳያስተምራት ራሷን በራሷ ያስተማረች ባለሙያ ናት” በማለት ነው።

" 'ቅቤው የጾም መሆኑን እንዴት እርግጠኛ መሆን እችላለሁ?' ብላን ነበር"

አልማዝ በርካታ ማስታወቂያዎች ብትሠራም በርካቶች ሸኖ ለጋን ያስታውሳሉ።

ያኔ የኃይል ሰዒድ ግሩፕ ኦፍ ካምፓኒ የምሥራቅ አፍሪካ ዳይሬክተር የነበረው ሪያድ አብዱልራዛቅ አሕመድ ነበር። በኢትዮጵያ፣ ኤርትራ፣ ሶማሊያና ጅቡቲ የነበረውን የድርጅቱን እንቅስቃሴ ከኢትዮጵያ ሆኖ ይቆጣጠር ነበር።

ለሸኖ ለጋ ቂቤ ማስታወቂያ አልማዝ ከተመረጠች በኋላ " 'ቅቤው የጾም መሆኑን እንዴት እርግጠኛ መሆን እችላለሁ? እኔ ክርስቲያን ነኝ። እንዴት ጾም እንደሌለው ሳላምን ማስታወቂያውን እሠራለሁ?' " ብላ እንደነበረ ሪያድ ያስታውሳል።

ማስታወቂያ ሠሪዎች አምቢ ካሉ በሌላ መለወጥ የተለመደ ቢሆንም አልማዝን ከመቀየር ግን ቅቤው የሚመረትበትን የየመን ፋብሪካ ለማስጎብኘት እንደወሰነ ይናገራል።

የመን በሚገኘው ፋብሪካ ቂቤው ሙሉ በሙሉ ከአትክልት እንደሚመረት ከተመለከተች በኋላ ማስታወቂያውን ለመሥራት ተስማማች።

ማስታወቂያው ለአንድ ዓመት ተኩል ያህል በቴሌቭዥን ተላልፏል። በተለያዩ አካባቢዎች ግዙፍ ቢልቦርዶች ተሰቅለውም ነበር።

የሸኖ ለጋ ቂቤ የኢትዮጵያ ቃና እንዲኖረው ለማድረግ በርካታ ገንዘብ እንደፈሰሰ የሚያስታውሰው ሪያድ፤ ማስታወቂያው ስኬታማ ለመሆኑና ምርቱም ለመሸጡ "የአልማዝ አሻራ አለበት" ይላል።

ድርጅቱ ከአቡወለድ ብስኩት ቀጥሎ ለዓመታዊ የማስታወቂያ ወጪ ከፍተኛ ገንዘብ የመደበው ለሸኖ ለጋ ቂቤ ነበር።

የሸኖ ለጋ ቂቤ ሽያጭ ውጤታማነት ሪያድ ወደ ድርጅቱ የዱባይ ዋና መሥሪያ ቤት እንዲዘዋወር ምክንያትም ሆኗል።

"አልማዝ የስኬት ታሪኬ ውስጥ አለች" ሲልም ይገልጻታል።

ድርጅቱ ምርቱ በስፋት ተቀባይነት ማግኘቱን ተከትሎ ለአልማዝ ሽልማት አበርክቶም ነበር።

በሐረርጌ ክፍል አገር አሰበ ተፈሪ ውስጥ በ1938 ዓ.ም የተወለደችው የአርቲስት አልማዝ ኃይሌ የአራት ልጆች እናት የነበረች ሲሆን፤ ያጋጠማትን ህመም ተከትሎ ህክምና ስትከታተል ቆይታ መስከረም 15/2013 ዓ.ም ነበር ከዚህ ዓለም በሞቶ የተለየችው።

የታዋቂዋ ሁለገብ አርቲስት የቀብር ሥነ ሥርዓት አዲስ አበባ ውስጥ በሚገኘው በመንበረ ፀባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል መስከረም 16/2013 ዓ.ም ተፈፅሟል።