በፈረንሳይ ከ2,500 በላይ ሰዎች በሕገ ወጥ ድግስ ላይ መሳተፋቸው ተነገረ

ታትሟል

ፈረንሳይ ውስጥ የፈረንጆችን አዲስ ዓመት አስታከው ከ2,500 በላይ ሰዎች በሕገ ወጥ ድግሶች መገኘታቸው ተገለጸ።

ኮሮናቫይረስ ከፍተኛ ስጋት ቢሆንም ሕገ ወጥ ድግሶቹ በብሪታኒ ግዛት ካለፈው ሐሙስ አንስቶ ሲካሄዱ ነበር።

ድግሱ ላይ ከተገኙት መካከል የዩናይትድ ኪንግደም እና የስፔን ዜጎች እንደሚገኙበት ፖሊስ ተናግሯል።

የድግሶቹ ታዳሚዎች ከፖሊስ ጋር መጋጨታቸውና መኪና ማቃጠላቸውም ተገልጿል። ፖሊሶች ድግሶቹን ለማስቆም ሲሞክሩ በታዳሚዎች ጥቃት ተሰንዝሮባቸዋል።

ከድግሶቹ በአንዱ የተገኘ ግለሰብ ለኤኤፍፒ እንደተናገረው አካላዊ ርቀት እምብዛም አልተጠበቀም ነበር ብሏል።

በእነዚህ ድግሶች ላይ የተገኙ ታዳሚዎች መኪናቸው ውስጥ እየተኙ ድግሱን መታደም እንደቀጠሉና እስከቀጣዩ ሳምንት ለመቆየት ያሰቡም እንዳሉ ተዘግቧል።

የፈረንሳይ የአገር ውስጥ ሚንስትር ጂራልድ ደርሜን ስለ ጉዳዩ ለመወያየት ስብሰባ ጠርተዋል።

ቢያንስ 200 ሰዎች በፖሊስ የቃል ማስጠንቀቂያ እንደተሰጣቸውና በአካባቢው ተሰብስበው የነበሩ መኪኖች መተላለፊያ ዘግተው እንደነበር ተናግረዋል።

ፈረንሳይ ከአዲስ ዓመት ጥቂት ቀናት ቀደም ብሎ የሰዓት እላፊ አውጃ እንዲሁም ኮሮናቫይረስን ለመከላከል የወጡ መርሆችን የሚያስፈጽሙ 100,000 ፖሊሶች አሰማርታም ነበር።

እነዚህ ፖሊሶች በተለያዩ ቦታዎች በድብቅ የሚካሄዱ ድግሶችን እንዲያስቆሙ ታዘዋል። ታዳሚዎችንና የድግሱን አዘጋጆች ለይተው እንዲያሳውቁም መመሪያ ተሰጥቷል።

በፈረንሳይ ከ2.6 ሚሊዮን በላይ ሰዎች በቫይረሱ ሲያዙ 64,892 ሞተዋል።