ክትባትና ውሃ አምራቹ ከእስያ ቁጥር አንድ ሀብታም ሆነ

ታትሟል

ዞንግ ሻንሻን የእስያ ሀብታሞች ዝርዝርን በግንባር ቀደምነት መምራት ጀምሯል።

ክትባት እና የታሸገ ውሃ ማምረቻ ባለቤት የሆነው ዞንግ፤ በዚህ ዓመት ሀብቱ ሰባት ቢሊየን ዶላር ጨምሯል።

የሕንዱን ሙከሽ አምባኒ እና የቻይናውን ጃክ ማ በልጦም የእስያ ቁጥር አንድ ባለ ጸጋ ሆኗል። አጠቃላይ ሀብቱ ወደ 77.8 ቢሊየን ዶላር ይጠጋል።

ይህም የዓለም 11ኛው ሀብታም እንደሚያደርገው የብሉምበርግ ቢሊየነር ኢንዴክስ ያሳያል።

“ብቸኛው ተኩላ” በሚል ቅጽል ስሙ የሚታወቀው ባለ ሀብት በጋዜጠኛነት፣ በእንጉዳይ እርሻና በጤናው ዘርፍም ሠርቷል።

ሚያዝያ ላይ ክትባት አምራቹ ቤጂንግ ዋንታይ ባዮሎጂካል ተቋምን በቻይና የአክስዮን ገበያ አቅርቧል። ከሦስት ወራት በኋላ ደግሞ ኖንግፊ ስፕሪንግ የተባለውን ውሃ አምራች ኩባንያ ለሆንግ ኮንግ የአክስዮን ገበያ አቅርቧል።

ከዚህ ቀደም የእስያ ቁጥር አንድ ሀብታም የአሊባባ መስራቹ ቻይናዊ ጃክ ማ ነበር።

ኖንግፊ ስፕሪንግ ሆንክ ኮንግ ውስጥ ከፍተኛ ተቀባይነት ካገኘ በኋላ የአክስዮን ዋጋው ወደ 155% አድጓል። የኮቪድ-19 ክትባትን ከሚሠሩ አንዱ የሆነው ቤጂንግ ዋንታይ ባዮሎጂካል የሼር ዋጋው ከ2,000% በላይ ደርሷል።

እነዚህ ተደማምረው ዞንግ ሻንሻን ከእስያ ሀብታሞች ቁንጮው እንዲሆን አስችለውታል። ብሉምበርግ እንደሚለው፤ በአጭር ጊዜ ውስጥ እንዲህ ያለ ሀብት ንብረት ያፈራ ሰው በታሪክ አልታየም።

በወረርሽኙ ወቅት የአማዞን መስራች ጄፍ ቤዞስን ጨምሮ ብዙ ሀብታሞች ጥሪታቸው ጨምሯል። የሕንዱ አምባኒ ሀብት ከ18.3 ቢሊየን ወደ 76.9 ቢሊየን ዶላር አድጓል።

በተቃራኒው የጃክ ማ ሀብት ጥቅምት ላይ ከ61.7 ቢሊየን ዶላር ወደ 51.2 ቢሊየን ወርዷል። አሊባባ በቻይና ባለሥልጣኖች ተደጋጋሚ ትንኮሳ ደርሶበታል።

ድርጅቱ በምርቶች መካከል ፍትሐዊ ያልሆነ ውድድር በማድረግ ምርመራ እየተደረገበት ሲሆን፤ አጋር ድርጅቱ አንት ግሩፕ ጥቅምት ላይ ከአክስዮን ሽያጭ ታግዷል።

አብዛኞቹ የቻይና አዳዲስ ቢሊየነሮች በቴክኖሎጂ ዘርፍ የተሰማሩ ናቸው።

በሌላ በኩል በቻይና እና በአሜሪካ መካከል ሁዋዌ፣ ቲክቶክ እና ዊቻትን በተመለከተ እየተባባሰ የመጣው ውጥረት የቻይና የአክስዮን ሽያጭ ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ አሳርፏል።