ኮሮናቫይረስ፡ ፈረንሳይ የአዲስ ዓመት ዋዜማ ድግሶችን ለመቆጣጠር 100 ሺህ ፖሊሶችን ልታሰማራ ነው

የፎቶው ባለመብት, Reuters
ፈረንሳይ በአዲስ ዓመት ዋዜማ ሰዎች እንዳይሰባሰቡና የበአል ድግስ እንዳያዘጋጁ ለመከልክል እንዲሁም የሰአት እላፊውን ተግባራዊ ለማድረግ 100 ሺ ወታደሮችን ልታሰማራ እንደሆነ አስታውቃለች።
ከዚህ በተጨማሪም የፖሊስ ኃይሉ በፈረንሳያውያን ዘንድ የተለመደውንና በአዲስ ዓመት ዋዜማ ዕለት መኪናዎችን የማቃጠል ስነ ስርአትን ለመከልከል እንደሚሰማራ ተገልጿል።
ፈረንሳይ እስካሁን 2.6 ሚሊየን ሰዎች በኮሮናቫይረስ መያዛቸውን የገለጸች ሲሆን ይህ ደግሞ ከዓለም አምስተኛ ደረጃ ላይ ያስቀምጣታል። የሟቾች ቁጥር ደግሞ 64 ሺ መድረሱን አገሪቱ ገልጻለች።
ልክ እንደ ሌሎች የአውሮፓ አገራት ፈረንሳይም አርብ ዕለት የሚከበረው አዲስ ዓመት ጸጥ ረጭ ብላ ታሳልፋለች።
የአገር ውስጥ ጉዳዮች ሚኒስትሩ ጄራልድ ዳርሚየን በመገበያያ ማዕከላትና ዋና ዋና ጎዳናዎች በደንብ ጎልቶ የሚወጣ የጥበቃ ኃይል እንዲሰማራ ያዘዙ ሲሆን የእንቅስቃሴ ገደቡም ቢሆን በጥብቅ መተግበር አለበት ብለዋል።
ፓሪስ ውስጥ ከሚሰሩት የከተማ ባቡሮች መካከል ግማሾቹ የሚዘጉ ሲሆን ሚኒስትሩ በሌሎች የአገሪቱ አካባቢዎችም በተመሳሳይ የጉዞ አማራጮች እንዲዘጉ ሀሳባቸውን አቀርበዋል።
ምንም እንኳን በቫይረሱ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር አሁንም እየጨመረ ቢሆንም ሚኒስትሩ በፈረንሳይ ሙሉ በሙሉ የእንቅስቃሴ ገደብ ማስቀመጥ አስፈላጊ አይደለም ሲሉ ተደምጠዋል።
ወታደሮቹ ማንኛውም አይነት በይፋም ይሁን በድብቅ የሚደረጉ ድግሶችን ለመበተን ተዘጋጅተዋል። በተጨማሪም በድግሶቹ ላይ የሚያዙ ሰዎች መቅጣትና አዘጋጆችን መለየት ዋነኛ ስራቸው ይሆናል።
ሚኒስትሩ ባስተላለፉት መልዕክት ዜጎች በአዲስ ዓመት ዋዜማ መኪና ማቃጠላቸውን እንዲያቆሙና በአሉን ቤታቸው ሆነው እንዲያከብሩ ጠይቀዋል።
በፈረንሳይ በአውሮፓውያኑ 2005 ላይ ፓሪስ ውስጥ ከተቀሰቀሰው አመጽ ጋር ተያይዞ በአዲስ ዓመት ዋዜማ መኪና ማቃጠል የተለመደ ስነ ስርአት ሆኗል።
ባለፈው ዓመት ብቻ 1457 መኪናዎች በእሳት እንዳልነበሩ ሆነው የተቃጠሉ ሲሆን ከሁለት ዓመት በፊት ደግሞ የተቃጠሉት መኪኖች ቁጥር 1290 እንደሆነ ተገልጿል።












