ጠላፊዎች የታዋቂ ሰዎችን የፕላስቲክ ቀዶ ሕክምና ፎቶ እንለቃለን ሲሉ ዛቱ

ጠላፊዎች የታዋቂ ሰዎችን 'የፕላስቲክ ቀዶ ሕክምና ፎቶ እንለቃለን' ሲሉ ዛቱ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ታትሟል

የበይነ መረብ ጠላፊዎች የታዋቂ ሰዎችን የፕላስቲክ ቀዶ ሕክምና ሂደት የሚያሳይ መረጃ እንለቃለን ሲሉ ዝተዋል።

ጠላፊዎቹ የታካሚዎችን የበፊትና የአሁን ፎቶ በመልቀቅ 'ጉድ እንሠራቸዋለን' እያሉ ነው።

'ዘ ሆስፒታል ግሩፕ' የተሰኘውና በታዋቂ ሰዎች ዘንድ እውቅና ያለው ድርጅት ጠላፊዎቹ ክፍያ ካልተፈፀማቸው መረጃዉን እንደሚያሾልኩ ዝተዋል ሲል አረጋግጧል።

ድርጅቱ ይህን ጉዳይ ለሚመለከተው ክፍል አሳውቅያለሁ ብሏል።

ሪቪል [REvil] በተሰኘ ስማቸው የሚታወቁት ጠላፊዎቹ 'ሚስጢራዊ የሆኑት' እኚህ ፎቶዎች ለተመልካች ብዙም ደስታ የሚሰጡ አይደሉም ብለዋል።

ጠላፊዎቹ በኮምፒውተር ልኬት 900 ጊጋባይት መጠን ያላቸው ፎቶዎች እጃችን ገብተዋል እያሉ ነው።

ዘ ሆስፒታል ግሩፕ በዩናይትድ ኪንግደም ቀዳሚው የክብደት ቅነሳና የፕላስቲክ ቀዶ ጥገና ሆስፒታል ነው።

ክብደት መቀነሻ ቀዶ ሕክምና፣ ጡት ማሳደግ፣ የጡት ጫፍ ማስተካከል እንዲሁም አፍንጫ ማረም ሆስፒታሉ በ11 ክሊኒኮቹ ከሚሰጣቸው አገልግሎቶቹ መካከል ናቸው።

ሆስፒታል በቀደመው ጊዜ በታዋቂ ሰዎች አማካይነት ማስታወቂያ ይሠራ ነበር።

ነገር ግን ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ይህንን ማድረግ አቁሟል።

በፈረንጆቹ 2009 'ቢግ ብራዘር' የተሰኘው የሰዎችን የዕለተ ተለት ሕይወት የሚያስቃኝ የቴሌቪዥን ፕሮግራም አባል የነበረችው አይዝሊን ዘ ሆስፒታል ግሩፕ ሄዳ ጡቷን እንዳሳደገች ተናግራ ነበር።

ታዋቂዋ ዘፋኝ ኬሪ ካቶና፣ ተዋናይት ቲና ማሎንና የቴሌቪዥን ኮከቡ ጆዊ ኤሴክስ ወደ ሆስፒታሉ ጎራ ብለው ሕክምና ካገኙ ታዋቂ ሰዎች መካከል ናቸው።

ሆስፒታሉ ደንበኞቹን ስለተፈጠረው ጉዳይ በኤሜይል አማካይነት ማሳቁንና በጣም ከባድ ሚስጥር ያላቸው ሰዎች አደጋ ላይ ሊሆኑ እንደሚችሉ እንደነገራቸው በለቀቀው መገለጫ አስታውቋል።

ጠላፊዎቹ እንለቃን ያሉት የአሁንና የቀድሞ ገፅታ የሚያሳይ ፎቶ የታካሚዎችን ማንነት ላያጋልጥ ይችላል ተብሏል።

ቢቢሲ ያነጋገረው አንድ ደንበኛ ሚስጢራዊ ፎቶዎቹ በጠላፊዎች እጅ ወድቆ እንዳይሆን ስጋት እንዳለው ይናገራል።

ሳይመን ሄይልስ የተሰኘው ደንበኛ ወደ ሆስፒታሉ ሄዱ ደረቱን አስቀንሶ መጥቷል።

ነገር ግን ኩባንያው ጠላፊዎቹ ገንዘብ ስለመጠያቃቸው እንዳላሳወቀው ተናግሯል።

"መረጃዎቻችን በጠላፊዎች እጅ ወድቀው ሊሆን እንደሚችል ተነግሮናል። ነገር ግን ዝርዝር መረጃ አልደረሰንም" ይላል።

በዓለም ዙሪያ ያሉ ጠላፊዎች መረጃ ከመዘበሩ በኋላ በምትኩ ገንዘብ ይጠይቃሉ። ይህ በሳይበር ቋንቋ 'ራንሰምዌር' ይባላል።

የመረጃ መረብ ደህንነት መሥሪያ ቤቶች መረጃቸው በጠላፊዎች የተወሰደባቸው ድርጅቶች ገንዘብ እንዳይከፍሉ ይመክራሉ።

መረጃ መዝባሪዎች በፈረንጆቹ 2020 ብቻ 25 ቢሊዮን ዶላር እንደመዘበሩ ይነገራል።

በዓለም በጣም ታዋቂ ከሆኑ መረጃ ጠላፊዎች መካከል ሪቪል አንዱ ነው። ከዚህ በፊትም ሁለት ትላልቅ ድርጅቶችን ጠልፎ ገንዘብ ተቀብሏል።