'ጌም ኦፍ ትሮንስ' የተሰኘውን 'ጌም' የፈጠረው ቻይናዊ ተመርዞ ሞተ

ቻይናዊው ቢሊዬኔር የ39 ዓመቱ ሊን ኪ የቪድዮ ጌም አምራች ኩባንያ የሆነው ዩዙ ሊቀ መንበርና ዋና ጌም አምራች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ታትሟል

ቻይናዊው ቢሊዬኔር በገና በዓል ተመርዞ መመቱን የሻንግሃይ ፖሊስ አስታወቀ።

የ39 ዓመቱ ሊን ኪ የቪድዮ ጌም አምራች ኩባንያ የሆነው ዩዙ ሊቀ መንበርና ዋና ጌም አምራች ነበር።

ድርጅቱ 'ጌም ኦፍ ትሮንስ፡ ዊንተር ኢዝ ካሚንግ' የተሰኘው የቪድዮ ጨዋታን ለገበያ በማቅረብ ነው ተወዳጅነት ያገኘው።

የሻንግሃይ ፖሊስ ያወጣው መግለጫ እንደሚጠቁመው የመጀመሪያ ስሙ ብቻ የተጠቀሰው ዙ የተባለው የሟቹ የሥራ ባልደረባ በመመረዝ ወንጀል ተጠርጥሯል።

ሊን፤ 6.8 ቢሊዬን ዬዋን ወይም 1 ቢሊዬን ዶላር ሃብት እንዳለው ይገመታል ሲል ሀሩን ቻይና ሪች ሊስት ዘግቧል።

በርካታ የድርጅቱ የቀድሞና የአሁን ሠራተኞች በዋና መሥሪያ ቤት ደጃፍ ላይ ተገኝተው ሃዘናቸውን ገልፀዋል።

ኩባንያው ልብ የሚነካ የሃዘን መግለጫ ዊቦ በተሰኘው የቻይና ማሕበራዊ ድር አምባ ላይ ለቋል።

"ቻዎ ወጣቱ" ይላል መግለጫው።

በሺዎች የሚቆጠሩ የዊቦ ተጠቃሚዎች ሃዘናቸው በአስተያየት መስጫ ሳጥኑ ላይ አኑረዋል።

290 ሚሊዮን የሚሆኑ ሰዎች ደግሞ በማሕብራዊ ድር አምባው አማካይነት የሃዘን መግለጫውን ተመልክተውታል።

'ጌም ኦፍ ትሮንስ' ከተሰኘው ጌም በተጨማሪ ዩዙ የተባለው የሟቹ ቢሊዬኔር ኩባንያ ቴንሴንት ከተሰኘው ጌም አምራች ጋር በመተባበር ብራውል ስታርስ የተባለ ታዋቂ የኮምፒውተር ጨዋታ አምርተዋል።

የሊን ኩባንያ ከዚህ በተጨማሪ ከአንድ የሳይንስ ልብ ወለድ ፊልም ሠሪ ድርጅት ጋር ይሠራል።

ነገር ግን ኩባንያ ወደ ፊልም ሥራ ለመሄድ ያደረገው ጥረት ብዙም የተሳካ አልነበረም።

ዩዙ ባለፈው መስከረም ኔትፊልክስ ከተሰኘው የአሜሪካ የበይነ መረብ ፊልም አከራይ ድርጅት ጋር አብሮ ለመሥራት ስምምነት ላይ ደርሶ ነበር።

ድርጅቶቹ የታዋቂውን ደራሱ ሊዩ ቺን መጽሐፍ ወደ ፊልም ለመቀየር ነው ዕቅዳቸው።

የቻይና ጋዜጦች ሊን በባልደረባው ዙ ሊመረዝ የቻለው ምናልባት በሥራ ቦታ ካላቸው አለመግባባት የተነሳ ነው እያሉ ነው።

ከአዳጊ ቻይናዊያን ባለሃብቶች መካከል አንዱ የነበረው ሊን የተወሰኑ መፅሐፍትም ፅፏል።