ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ቦይንግ 737 ማክስ አውሮፕላን የሞተር ችግር ገጥሞት እንዲያርፍ ተገደደ
የኤር ካናዳ ንብረት የሆነ ቦይንግ 737 ማክስ አውሮፕላን ድንገተኛ የሞተር ችግር ገጥሞት እንዲያርፍ መገደዱ ተገለጸ።
ኤር ካናዳ አየር መንገድ እንዳስታወቀው፤ አውሮፕላኑ ከአሪዞና ወደ ሞንትሪያል ሊጓዝ ነበር። ነገር ግን በረራ ጀምሮ ወዲያውኑ እንዲያርፍ ተደርጓል።
አውሮፕላኑ ሦስት ሠራተኞችን አሳፍሮ የነበረ ሲሆን፤ በሰላም ማረፉ ተገልጿል።
737 ማክስ አውሮፕላን የኢትዮጵያ አየር መንገድና የኢንዶኔዥያ የአውሮፕላን አደጋን ተከትሎ አምና ከበረራ ታግዶ እንደነበር ይታወሳል።
በዚህ ወር መባቻ ግን በድጋሚ ወደ በረራ እንዲመለስ ፍቃድ ተሰጥቶታል።
በኢትዮጵያ እና በኢንዶኔዥያ በደረሱ የአውሮፕላን አደጋዎች ባጠቃላይ 346 ሰዎች ሞተዋል።
አደጋዎቹ የተከሰቱት በአውሮፕላኑ የበረራ መተግበሪያ ችግር ሳቢያ እንደሆነም ተጠቁሟል።
ትላንት ስለገጠመው የሞተር እክል ያስረዳው ኤር ካናዳ "አውሮፕላን አብራሪዎቹ ስለ ሞተሩ ሁኔታ ጥቆማ (ኖቲፊኬሽን) ሲደርሳቸው ሞተሩን ለማጥፋት ወሰኑ" ብሏል።
የቤልጄም አቪየሽን የዜና ድረ ገጽ እንዳለው፤ አብራሪዎቹ በአውሮፕላኑ ቀኝ ሞተር አካባቢ ችግር ሲያስተውሉ ነው በረራውን አቋርጠው አውሮፕላኑን ለማሳረፍ የወሰኑት።
ቦይንግ ከኢትዮጵያ እና ከኢንዶኔዥያ የአውሮፕላን አደጋ በኋላ የበረራ መቆጣጠሪያ መተግበሪያውን ጨምሮ በተለያዩ ክፍሎች ላይ ማሻሻያ እንዳደረገ ይፋ አድርጎ ነበር።
ከሦስት ሳምንት በፊት የቦይንግ 737 ማክስ አውሮፕላን በረራ እንዲጀምር ብራዚል መፍቀዷ አይዘነጋም።