የአሜሪካ ሴኔት ቦይንግ አብራሪዎችን በተሳሳተ መልኩ አሰልጥኖ ነበር አለ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የአሜሪካ ሴኔት መርማሪዎች የአውሮፕላን አምራቹ ቦይንግ የ737 ማክስ አውሮፕላኖችን የሚፈትሹ አብራሪዎችን 'ተገቢ ባልሆነ መልኩ' ስልጠና እንዲያገኙ አድርጓል ሲሉ ከሰሱ።
በወራት ልዩነት ሁለት አደጋዎች ማጋጠማቸውን ተከትሎ ቦይንግ 737 ማክስ አውሮፕላኖች በአውሮፓውያኑ መጋቢት 2019 ላይ እንዳያበሩ ታግደው ነበር።
መርማሪዎቹ እንደሚሉት ቦይንግ እና የፌደራል አቪዬሽን አስተዳደር (FAA) በመመሳጠር ስለአውሮፕላኖቹ ወሳኝ መረጃዎችን ሆን ብለው ለመደበቅ ሞክረዋል።
ቦይንግ በበኩሉ በምርመራው የተገኙትን መረጃዎች በሙሉ እየተመለከታቸው እንደሆነና ጉዳዩን በጥብቅ የሚያው እንደሆነ የገለጸ ሲሆን የፌደራል አቪዬሽን አስተዳደር በበኩሉ ምንም ስህተት አልሰራሁም ብሎ ነበር።
ከኢትዮጵያ ወደ ኬንያ ሲበር በነበረው ቦይንግ 737 ማክስ አውሮፕን የደረሰው አደጋ ከመከሰቱ በፊት የአሜሪካ አውሮፕላን አብራሪዎች ቡድን በዚህ መሰል አውሮፕላኖች የደህንነት ስጋት እንዳለ ለኩባንያው አሳውቀው እንደነበር መገለጹ ይታወሳል።
ግንቦት 2019 ላይ በቦይንግ 737 ማክስ አውሮፕላን ከዚህ ቀደም በኢንዶኔዥያ ከደረሰው አደጋ በኋላ ኤምካስ (MCAS) ተብሎ በሚጠራው መቆጣጠሪያ ስርዓት ላይ ችግር እንደነበረበትና በአፋጣኝ እንዲፈታ አሳስበው እንደነበርም ተገልጾ ነበር።
በወቅቱ ቦይንግ ግን አብራሪዎች ያነሱትን ጥያቄ ወደጎን በመተው ወደ ፊት የበረራ መቆጣጠሪያ ሶፍትዌሩን ለማስተካከል ቃል መግባቱ ተገልጿል።
የፌደራል አቪዬሽን አስተዳደር የአሜሪካ ሴኔት በመረጃ የልተደገፈ ውንጀላ እያደረገ እንደሆነ በመግለጽ በ737 ማክስ አውሮፕላኖች ላይ ያደረገው ምርመራ በጥልቀት የተካሄደ መሆኑን አስታውቋል።
ባለፈው ዓመት ጥቅምት ወር ላይ የአንዶኔዥያው ላየን ኤይር ንብረት የሆነው 737 ማክስ 8 ተከስክሶ በአውሮፕላኑ ተሳፍረው ነበሩት 189 ሰዎች ማለቃቸው ይታወሳል።
አደጋው በተከሰተበት ወቅት የኢንዶኔዥያ የአደጋ ጊዜ ሠራተኞች አደጋው አውሮፕላኑ ላይ በነበረ እክል ምክንያት ነው የተከሰተው ቢሉም ድርጅቱ እጄ የለበትም ማለቱ ይታወሳል።
ከአምስት ወራት በኋላ ደግሞ መጋቢት 1 ቀን ከኢትዮጵያ ወደ ኬንያ ሲበር የነበረው ቦይንግ 737 ማክስ 8 አውሮፕላን አደጋ ለ157 ሰዎች ህይወት መቀጠፍ ምክንያት ሆኗል።
ትናንት አርብ ዕለት የሴኔት መርማሪ ኮሚቴው ባወጣው ሪፖርት ላይ ከድርጅቱ በሚስጥራዊ መንገድ አገኘሁት ባለው መረጃ የፌደራል አቪዬሽን አስተዳደር እና ቦይንግ ከምርመራው ቀደም ብለው የምርመራው ውጤት እነሱ በሚፈልጉት መንገድ እንዲሆን አድርገዋል ብሏል።
ይህ ሪፖርት የአሜሪካ ፌደራል አቪዬሽን አስተዳደር ባሳለፍነው ወር ቦይንግ 737 ማክስ አውሮፕላኖች በድጋሚ መብረር እንዲጀምሩ ከፈቀደ በኋላ መሆኑ ቦይንግን ያስደሰተው አይመስልም።
በያዝነው ወር መጀመሪያ አካባቢ የብራዚሉ ጎል አየር መንገድ ቦይንግ 737 ማክስ አውሮፕላንን ወደ በረራ እንደሚመልስ ማስታወቁ የሚታወስ ነው።
የብራዚል ግዙፉ አየር መንገድ ጎል እንዳለው፤ 140 የሚሆኑ አውሮፕላን አብራሪዎቹ በአውሮፕላኑ አሜሪካ ውስጥ ሥልጠና ወስደዋል።
ሰባት 737 ማክስ አውሮፕላኖቹን ለ27 የአገር ውስጥ መዳረሻዎች ማዘጋጀቱን አየር መንገዱ ገልጿል። እስካሁን 737 ማክስ ወደ በረራ እንዲመለስ የፈቀዱት አሜሪካ እና ብራዚል ናቸው።












