ኮቪድ-19 ፡ የአሜሪካው ምክትል ፕሬዚደንት ማይክ ፔንስ የኮቪድ-19 ክትባት ተከተቡ

ማይክ ፔንስ

የፎቶው ባለመብት, Reuters

ታትሟል

የአሜሪካው ምክትል ፕሬዚደንት ማይክ ፔንስ በቴሌቪዥን የቀጥታ ሥርጭት እየታዩ የኮሮናቫይረስ ክትባት ተከተቡ።

ምክትል ፕሬዚደንቱ ለተመልካቾችና ለዶክተሮች "ምንም ነገር አልተሰማኝም" ብለዋል።

ማይክ ፔንስ በቀጥታ ሥርጭት እየታዩ የመከተባቸው ዓላማ የክትባቱን ደህንነትና ውጤታማነት ለማስተዋወቅና በአሜሪካ ሕዝቦች ዘንድ መተማመንን ለመፍጠር እንደሆነ ዋይት ሃውስ አስታውቋል።

በዚህ በዋይት ሃውስ በተሰናዳው ዝግጅት የምክትል ፕሬዚደንቱ ባለቤት እና የጤና ጥበቃ ጠቅላይ ኃላፊ [ሰርጅን ጀነራል] ጀሮሜ አዳምስም ክትባቱን ወስደዋል።

የ61 ዓመቱ ማይክ ፔንስ ከባለቤታቸው ካረን እና አዳምስ ጋር የመጀመሪያዎቹን ሁለት ዶዝ የፋይዘር/ ባዮንቴክ ክትባት የወሰዱት ዛሬ ከቀኑ 10 ሰዓት ነው።

አሜሪካ 95 በመቶ በሽታውን ይከላከላል የተባለውን የፋይዘር/ ባዮንቴክ ክትባት መከተብ የጀመረችው ባሳለፍነው ሰኞ ነበር።

የመጀመሪያ ሦስት ሚሊየን ዶዝ [መጠን] ክትባቶችም በ50 የአገሪቷ ግዛቶች ተሰራጭተዋል።

ጥቅምት ወር ላይ በኮሮናቫይረስ ተይዘው በሆስፒታል ሕክምና ከተደረገላቸው በኋላ ያገገሙት ማይክ ፔንስ፤ ክትባቱን ለመውሰድ ጊዜ አስቀምጠው እንዳልነበርና በተገቢው ጊዜ ግን ለመከተብ በጉጉት ሲጠባበቁ እንደነበር ተናግረዋል።

ዘጋቢዎች እንደሚሉት በርካታ ደጋፊዎቻቸው ስለክትባቱ ደህንነትና ውጤታማነት ጥርጣሬ አላቸው።

ለኮቪድ-19 ተጋላጭ ከሆኑት የሚመደቡት የ78 ዓመቱ ተመራጩ ፕሬዚደንት ጆ ባይደንም በሚቀጥለው ሳምንት ይከተባሉ ተብሎ ይጠበቃል።

ጆ ባይደን በመጭው በፈረንጆቹ ጥር 20 ወር በዋይት ሃውስ ሥራቸውን ሲጀምሩ በመጀመሪያዎቹ 100 ቀናት፤ 100 ሚሊየን የአሜሪካ ሕዝቦችን ለመከተብ ግብ አስቀምጠዋል።

ይህ ቁጥር የአሜሪካ ሕዝብ አንድ ሦስተኛ እንደሆነ ይገመታል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ በሞደርና የሚመረተው ሁለተኛው ክትባት በባለሙያዎች ተቀባይነት ካገኘ በኋላ ለድንገተኛ ጊዜ እንዲውል ፈቃድ ለማግኘት እየተቃረበ ነው።

በአሜሪካ ከ310 ሺህ በላይ ሰዎች በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ሳቢያ ሕይወታቸው ያለፈ ሲሆን፤ በዓለማችን ከፍተኛ በቫይረሱ የተያዙ እና የሞቱ ሰዎች ቁጥር ከተመዘገበባቸው አገራት ግንባር ቀደሟ ናት።