ኮሮናቫይረስ፡ ሕንድ ክትባቱን በጥር ወር መስጠት ልትጀምር ነው

የፎቶው ባለመብት, Reuters
ሕንድ በመጪው ጥር ወር ላይ የኮቪድ-19 ክትባት ለዜጎቿ ለመስጠት ማሰቧን የአገሪቱ የፌደራል ኃላፊዎች ለቢቢሲ ተናግረዋል።
ማንነታቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉት ኃላፊዎች እንዳሉት ጥቂት ክትባቶች በቅርቡ ለድንገተኛ ጥቅም ላይ እንዲውሉ ከመድሀኒት ቁጥጥር ባለስልጣን ፈቃድ የማግኘት ዕድላቸው ከፍተኛ ነው።
እስካሁን ሁለት ክትባት አምራች ኩባንያዎች ክትባቱን ለማቅረብ ጥያቄ ያቀረቡ ሲሆን ሌሎች ተጨማሪ ስድስት ክትባቶች ደግሞ በመጨረሻ የሙከራ ደረጃ ላይ ይገኛሉ ተብሏል።
እስከ ፈረንጆቹ አዲስ ዓመት ሐምሌ ወር ድረስ ደግሞ 300 ሚሊየን ሰዎችን ለመከተብ እቅድ መያዙ ተገልጿል።
ሕንድ በኮሮረናቫይረስ የተያዙባት ሰዎች ቁጥር 10 ሚሊየን የተጠጋ ሲሆን ከ144 ሺ በላይ ሰዎች ደግሞ በዚሁ ወረርሽኝ ሳቢያ ሕይወታቸውን እንዳጡ ተረጋግጧል።
'በሴረም ኢንስትትዩት ኦፍ ኢንዲያ' የበለጸገው 'ኮቪሺልድ' የተባለው ክትባት ፈቃድ ከጠየቁት መካከል አንዱ ሲሆን ከእንግሊዙ መድሀኒት አምራች ኩባንያ አስትራዜኔካ ጋር በጥመረት የተሰራ ነው።
ሌላኛው ፈቃድ ለማግኘት እየተጠባበቀ የሚገኘው 'ኮቫክሲን' የተባለው ክትባት ሲሆን በባሃራት ባዮቴክ እና 'በኢንዲያ ካውንስል ኦፍ ሜዲካል ሪሰርች' ጥምረት የተዘጋጀ ነው ተብሏል።
ሀሳባቸውን ለቢቢሲ ያካፈሉት ባለስልጣናት ከሰሞኑ ሕንድ በመላው ዓለም ከሚገኙ በርካታ ክትባት አምራቾች በሚሊየኖች የሚቆጠሩ ክትባቶችን ቀድማ አዛለች በሚል የተሰራጨው መረጃ ሐሰት ነው ብለዋል።
''መንግስት አገር በቀል ከሆኑ ክትባት አምራቾች ጋር በቅርበት እየሰራ ነው። ስለደህንነትና መሟላት ስላለባቸው ቅድመ ሁኔታዎች መረጃ እየተለዋወጡ ነው'' ብለዋል።
ቀደም ብለው የተጠቀሱት ሁለቱ ክትባት አምራቾች ብቻቸውን በአንድ ወር ውስጥ 65 ሚሊየን የክትባት ብልቃጦችን የማምረት አቅም ያላቸው ሲሆን ክትባቶቹን በቀላሉ ለማከፋፈልም በቂ አቅም አላቸው።
እንደ የፌደራል ጤና ኃላፊዎቹ ከሆነ ከጥር እስከ ነሀሴ ወር ድረስ 300 ሚሊየን ሕንዳውያን ክትባቱን ያገኛሉ። 10 ሚሊየን የሚሆኑ የጤና ባለሙያዎች ቅድሚያ የሚሰጣቸው ሲሆን በመቀጠል ፖሊሶች፣ ወታደሮችና ሌሎች ወሳኝ ስራዎችን የሚሰሩ ዜጎች ይከተባሉ።
ከነዚህ ሰዎች በመቀጠል ክትባቱን ለማግኘት ዕድል ይሰጣቸዋል የተባሉት ደግሞ ተያያዥ የጤና ችግሮች ያሉባቸው እድሜያቸው ከ50 ዓመት በላይ የሆኑ ሰዎች ናቸው።
ባለስልጣናቱ እንደሚሉት በአገሪቱ ካሉት 223 ሺህ ነርሶችና አዋላጅ ነርሶች ውስጥ 154 ሺ የሚሆኑት በክትባቱ ሂደት ላይ የሚሳተፉ ሲሆን ተመራቂ የነርሲንግ ተማሪዎችም እንዲሳተፉ ይደረጋል።
እስካሁን 29 ሺ የሚሆኑ ክትባቶቹ የሚቀመጡባቸው ሁሉም ነገር የተሟላላቸው መጋዘኖችም ተዘጋጅተዋል።















