የሞደርና ክትባት በአሜሪካ እውቅና ለማግኘት ተቃርቧል

መርፌ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ታትሟል

የፋይዘርን ክትባት ወደ ተግባር መግባት ተከትሎ በአሜሪካ 2ኛው ክትባት ሞደርና ፍቱን ነው ተብሏል።

ሞደርና ክትባት 94 በመቶ አስተማማኝ መሆኑ ተረጋግጦለታል። ይህም በቅርቡ ወደ ትግበራ እንዲገባ መንገድ የሚጠርግለት ነው ተብሏል።

ክትባቱን የመረመረው የአሜሪካ የምግብና መድኃኒት ቁጥጥር ባለሥልጣን ክትባቱ ፍቱን ነው በማለት ፋይዘርን ተከትሎ በአሜሪካ 2ኛው እውቅና ያገኘ ክትባት ያደርገዋል።

ይህ መልካም ዜና የተሰማው አሜሪካኖች የፋይዘርና ባዮንቴክ ክትባትን መቀበል በጀመሩ ማግስት ነው።

በኮሮናቫይረስ ክፉኛ በተጠቃችው አሜሪካ 300ሺ አሜሪካዊያን በተህዋሲው መሞታቸውን የጆን ሆፕኪንስ ዩኒቨረስቲ መረጃ ያስረዳል።

ሞደርና በምግብና መድኃኒት ባለሥልጣን ሳይንቲስቶች ዘንድ ለሁለት ቀናት በጥልቅ ከተመረመረ በኋላ ነው ፍቱን ነው የሚል ሰርተፍኬት ያገኘው።

54 ገጾችን የያዘው ሰነድ እንደሚለው ሞደርና ይህ ነው የሚባል ጉልህ የጎንዮሽ ጉዳት የለውም።

በዚህ ሳምንት መጨረሻ በሌሎች የሳይንቲስቶች ቡድን ከተመረመረ በኋላ የምግብና መድኃኒት ቁጥጥር ባለሥልጣን ዳይሬክተር ይፈርሙበታል።

ከዚህ በኋላ 24 ሰዓት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ክትባቱን ወደተለያዩ ቦታዎች መጫንና ማድረስ ይጀመራል።

የምግብና መድኃኒት ቁጥጥር ባለሥልጣን 30ሺህ በሆኑ ሰዎች ላይ የተሠራውን ጥናት መርምሮ እንዳለው ከሆን ሞደርና 94.1% የፍቱንነት ምጣኔ አለው ብሏል።

ክትባቱ የጎንዮሽ ጉዳቱ ትኩሳት፣ የራስ ምታት እና መጠነኛ የጡንቻና የአጥንት መገጣጠምያ ህመም ብቻ ናቸው።

ባለፈው ሳምንት የአሜሪካ የምግብና መድኃኒት ቁጥጥር ባለሥልጣን ለፋይዘር ክትባትም ተመሳሳይ የጎንዮሽ ጉዳቶችን መስጠቱ ይታወሳል።

ሞደርና በአውሮፓውያኑ 2010 የተመሰረተ ሲሆን በምግብና መድኃኒት ቁጥጥር ባለሥልጣን አንድም መድኃኒት ጸድቆለት አያውቅም።

ሞደርና ከዜሮ በታች 20 ሴትንት ግሬድ ማቀዝቀዣን ይፈልጋል። ይህም ከመደበኛ ማቀዝቀዣ ብዙም የተለየ አይደለም። የፋይዘር ክትባት ግን ለማጓጓዝ ከዜሮ በታች -75C ማቀዝቀዣ ስለሚፈልግ ፈታኝ ነው ተብሏል።

ሞደርና ክትባት ልክ እንደ ፋይዘር ሁሉ ከ28 ቀናት በኋላ 2ኛ ጠብታ መውሰድን ይሻል። ፋይዘር በአሁኑ ሰዓት በጀርመንና ቤልጂየምም እየተመረተ ይገኛል።

አሜሪካ የሞደርናን 200 ሚሊዮን ብልቃጦችን ለመግዛት ተስማምታለች። ከዚህ ውስጥ 6 ሚሊዮኑ ክትባቱ በጸደቀ በ24 ሰዓት ውስጥ ይሰራጫል። ካናዳ በበኩሏ 2 ሚሊዮን ሞደርናን ለመግዛት ፈቅዳለች። ታላቋ ብሪታኒያ 7 ሚሊዮን የሞደርና ብልቃጦችን ቀደም ብላ ነው ያዘዘችው።

የአውሮጳ ኅብረት በበኩሉ 80 ሚሊዮን ብልቃጦችን ለመግዛት ተፈራርሟል።ጃፓን 50 ሚሊዮን፥ ደቡብ ኮሪያ 20 ሚሊዮን ስዊዘርላንድ 7 ሚሊዮን ብልቃጦችን ከሞደርና ለመግዛት ፊርማቸውን አኑረዋል።