ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የስፔን ፖሊስ እየተበዘበዙ የነበሩ 21 ስደተኞችን ማዳኑን ገለፀ
የስፔን ፖሊስ በግዳጅ ለረዥም ሰዓታት እንዲሰሩ ተገደው የነበሩ 21 ስደተኞች የጉልበት ሠራተኞችኝ ማዳን ችያለሁ ብሏል።
ሠራተኞቹ በአንድ የልብስ መጋዘን ውስጥ ለሥራ ፍፁም አመቺ ባልሆነ ሁኔታ ሲሰሩ ነበር ተብሏል።
የጉልበት ሠራተኞቹ ሲለቀቁ የሚያሳይ አንድ ተንቅሳቃሽ ምስል ተለቋል።
ምስሉ ላይ በርካታ ሰዎች ከትላልቅ የልብስ ማከማቻ ሳጥኖች ጀርባ ሲወጡ ያሳያል። ክፍሉ በልብስ ማከማቻ ሳጥኖች የተሸፈነ ስለነበር ሥፍራው በውል አይታወቅም።
በደቡብ ምስራቃዊቷ የስፔን ግዛት ሙርሺያ ያለውን ይህን መጋዘን የሚያስተዳድሩ አባትና ሁለት ልጆች በፖሊስ ቁጥጥር ሥር ውለዋል።
ፖሊስ እንደሚለው አባትና ልጆች ልብሱን አምርተው ለአፍሪካ ሃገራት እያከፋፈሉ ይቸበችባሉ።
የሃገሪቱ ባለሥልጣናት ጉዳዩን በሚመለከት ባወጡት መግለጫ ስደተኞቹ የጉልበት ሠራተኞች በቀን ከልክ በላይ ለሆነ ሰዓት እንደሚሰሩ አሳውቀዋል።
አልፎም የሥራ ቦታዎች በፍፁም አመቺ ያልሆነ ነው ብለዋል።
ስደተኞቹ የጉልበት ሠራተኞች በሰዓት ከ2 ዩሮ በታች ብቻ ነበር ሲከፈላቸው የነበረው ይላሉ የስፔን ባለሥልጣናት።
መግለጫው አክሎ እንደሚገልፀው ፖሊስ ሠራተኞቹን ለመታደግ ወደ ሥፍራው ሄዶ ቦታውን በበረበረ ጊዜ የፋብሪካው አስተዳዳሪ ሠራተኞቹ ላይ እየጮኸ ተደበቁ ሲላቸው ነበር።
ፖሊስ እንደሚለው ፋብሪካው ለመሰል ጊዜ የሚያገለግል በልብስ ክምር የተሸፈኑ ክፍሎች አዘጋጅቶ ነበር።
ቀጣሪዎቹ በስደት ወደ ስፔን የመጡ ሰዎችን እየመለመሉ ለጉልበት ብዝበዛ ዳርገዋቸዋል ይላል ፖሊስ።
መግለጫው በሥራ ቦታ ምንም ዓይነት ለአደጋ ጊዜ የሚሆን ማምለጫም ሆነ ንፅህናን ለመጠበቅ የሚያስችል ምቹ ሁኔታ አልነበረም።
በቁጥጥር ሥር የዋሉት ሶስቱ ሰዎች ካርታጌና በሚገኝ አንድ ፍርድ ቤት ይቀርባሉ ተብሎ ይጠበቃል።
ስፔን ውስጥ የሚኖሩ የውጭ ሃገራት የጉልበት ወይም የቤት ሠራተኞች ብዙ ጊዜ የጉልበት ብዝበዛ ይደርስብናል ሲሉ ያማራሉ።