ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ምዕራብ አፍሪካዊቷ ጋና ፕሬዝደንታዊ ምርጫዋን እያካሄደች ነው
ጋናውያን አዲስ ፕሬዝደንት ለመምረጥ ዛሬ ወደ ምርጫ ጣቢያዎች ሲጎርፉ ውለዋል።
ከፕሬዝደንታዊው ምርጫ በተጨማሪ መራጮች ለ275 የሕዝብ እንደራሴዎች ድምፃቸውን ይሰጣሉ።
በስልጣን ላይ የሚገኙት ፕሬዝደንት ናና አኩፎ አዶ ለሁለተኛ ጊዜ ለመመረጥ ዕጩ ሆነው ቀርበዋል።
ተቀናቃኛቸው ደግሞ ባለፈው ምርጫ ወቅት በቅስቀሳ ሂደት ላይ በተሰራ ስህተት በድጋሚ ሳልመረጥ ቀርቻለሁ የሚሉት የቀድሞው ፕሬዝደንት ጆን ማሃማ ናቸው።
ከሁለቱ ተቀናቃኞች በተጨማሪ 11 ዕጩዎች ቀጣይ የጋና ፕሬዝደንት ለመሆን እየተፋለሙ ይገኛሉ።
ጋና የጥምር ፖለቲካ ፓርቲዎች ዴሞክራሲን ተግባራዊ ማድረግ ከጀመረች ወዲህ ይህ ስምንተኛው ፕሬዝደንታዊ ምርጫ ነው።
የምርጫ ጣቢያዎች በአገሪቱ ሰዓት አቆጣጠር ከጥዋቱ 1 ሰዓት ጀምሮ ተከፍተው መራጮችን በማስተናገድ ላይ ይገኛሉ።
ጣቢያዎቹ የሚዘጉት አመሻሽ 11 ሰዓት ላይ እንደሆነ ተገልጿል።
በዚህኛው ዙር ምርጫ 17 ሚሊዮን ጋናውያን ድምፃቸውን ለመስጠት ተመዝግበዋል።
ምርጫውን በበላይነት የሚመራው የአገሪቱ ምርጫ ኮሚሽን የኮቪድ-19 ሕግጋት ተግባራዊ እያደረገ ምርጫውን እንደሚቆጣጠር አሳውቋል።
የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ያላደረጉ መራጭች ድምፅ እንዲሰጡ አይፈቀድላቸውም ተብሏል።
ሰዎች ድምፃቸውን ከሰጡ በኋላ ቀጥታ ወደ መኖሪያ ቤታቸው እንዲመለሱ ተመክረዋል።
ምርጫውን ለመዘገብ ጋና የሚገኘው የቢቢሲው ቶማስ ናዲ ሰዎች በጣም በንጋት ለምርጫ ተሰልፈው እንደተመለከተ ዘግቧል።
አንዳንድ ሰዎች ተራቸው እንዳይያዝባቸው ድንጋይ ደርደረው ወረፋ በማስያዝ እንደሄዱም ታዝቧል።
የጋና ምርጫ ኮሚሽን የዘንድሮው ምርጫ ሰላማዊ እንዲሆን ጥሪ አስተላልፏል።
ከዚህ በፊት በፖለቲከኞች ተቀጥረዋል የተባሉ ሰዎች አመፅ አነሳስተው ወከባ የተነሳባቸው ምርጫዎች ነበሩ።
ነገር ግን ኮሚሽኑ ባለፈው ዓመት ምርጫን ሰበብ አድርገው አመፅ የሚያነሳሱ በትንሹ በ10 ዓመት ይቀጣሉ ብሏል።
ጋና በፈረንጆቹ ከ1992 ጀምሮ አምስት ፕሬዝደንቶችን አይታለች። ሦስት ጊዜ ደግሞ ፕሬዝደንቶቿ በሰላም ሥልጣናቸውን አስክበዋል።
በአፍረካ ውስጥ ተአማኒ ምርጫዎችን ካደረጉ አገራት መካከል ምዕራብ አፍሪካዊቷ ጋና ዴሞክራሲያዊት አገር እየተባለች በተደጋጋሚ ትሞካሻለች።