ቴክኖሎጂ ፡ ፌስቡክ ለስደተኞች ሥራ ሰጥቷል ስትል አሜሪካ ከሰሰች

ማርክ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ታትሟል

የአሜሪካ ፍትህ ሚኒስቴር ፌስቡክ ለስደተኞች ቅድሚያ በመስጠት አሜሪካውያንን በድሏል ሲል ከሷል።

ክሱ እንደሚያመለክተው ማሕበራዊ ድር አምባው 2600 የሚሆኑ ክፍት የሥራ መደቦች ላይ አሜሪካውያን መቅጠር ሲገባው አልቀጠረም።

በምትኩ ጊዜያዊ ቪዛ ላላቸው የውጭ ሃገራት ዜጋዎች ሥራው ተሰጥቷል ሲል የክስ መዝገቡ አስነብቧል።

ፌስቡክ የቀረበበትን ክስ ቢያጣጥልም ከፍትህ ሚኒስቴር ጋር በትብብር እየሠራ እንደሆነ ግን ተናግሯል።

ፌስቡክና ሌሎች ግዙፍ የቴክኖሎጂ ኩባንያዎች ኤች-1ቢ የተሰኘውን ቪዛ በመጠቀም ከሌሎች ሃገራት ምጡቅ አእምሮ ያላቸውን ሰዎች ያስመጣሉ።

ሐሙስ ዕለት ፍትህ ሚኒስቴር ያቀረበው ክስ ፌስቡክ ሆን ብሎ የሥራ ቅጥር ሲያወጣ ኤች-1ቢ ቪዛ ላላቸው ሰዎች እንዲሆን አድርጎ ነው ይላል።

ሚኒስቴሩ ለሁለት ዓመት ምርመራ ካደረግኩ በኋላ ነው ክሱን የመሠረትኩት ብሏል።

ክሱ ተሰሚነት የሚያገኝ ከሆነ ፌስቡክ "ሥራ ለነፈጋቸው አሜሪካዊያን" መክፈል የነበረበትን ያክል ገንዘብ ሊቀጣ ይችላል።

የሚኒስቴሩ ሠራተኞ የሆኑት ጠበቃ ኤሪክ ድራይባንድ የቴክኖሎጂ ኩባንያዎች መሰል ሕገ ወጥ የሆነ ተግባር ከመከወን እንዲቆጠቡ አሳስበዋል።

የባይደን የቤት ሥራ

እስካሁን ሽንፈታቸውን በፀጋ ያልተቀበሉት ዶናልድ ትራምፕ ለመጪው የባይደን አስተዳደር የተዝረከረከ ሥራ ትተው ለማለፍ የፈለጉ ይመስላል ትላለች የቢቢሲዋ ተንታኝ ሳሚራ ሁሴን።

ትራምፕ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ አዳዲስ ሕግጋትና ፖሊሲዎች እያወጡ ይገኛሉ።

ባለፉት አራት ዓመታት ኤች-1ቢ ቪዛ ያላቸው ሰዎችን ኩባንያዎች እንዳይቀጥሩ ትራምፕ ያልቆፈሩት ድንጋይ የለም።

ምንም እንኳ የቴክኖሎጂ ኩባንያዎች በመሰል የቪዛ ዓይነት ሰዎችን በመቅጠር የታወቁ ቢሆኑም ትራምፕ ግን ቅድሚያ ለአሜሪካዊያን በሚለው አጀንዳቸው አላፈናፍንም ብለዋቸዋል።

ፌስቡክ ላይ የቀፈበውም ክስ ይህን የተንተራሰ ነው።

ትራምፕ ከቴክኖሎጂ ኩባንያዎች ጋር ያላቸወ ግንኙነት የሻከረ ነው።

ፌስቡክን የመሰሉ ግዙፍ ማሕበራዊ ድር አምባዎች ሃሰተኛ መረጃ በአምባቸው እንዲሰራጭ ፈቅደዋል እየተባሉ ይተቻሉ።

ይህን ትችት የሚያሰሙት ዴሞክራቶች ብቻ ሳይሆኑ ሪፐብሊካንም ጭምር ናቸው።

ፌስቡክ ግን ይህን ክስ ያጣጥላል። ተጠቃሚዎች እንደፈቀዳቸው እንዲጠቀሙ ልንፈቅድ ይገባል ይላል።