የአሜሪካ ምርጫ 2020 ፡ የትራምፕ የቅርብ ሰው "ምርጫው አልተጭበረበረም" አሉ

ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ዊሊያም ባር

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የምስሉ መግለጫ, ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ዊሊያም ባር
ታትሟል

የአሜሪካ ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ዊሊያም ባር የአገሪቱ ፍትህ መስሪያ ቤት ምርጫው ተጭበርብሯል ብሎ እንደማያምን አሳወቁ።

ዐቃቤ ሕጉ "መሥሪያ ቤቴ የፕሬዝደንት ትራምፕን ክስ የሚደግፍ ማስረጃ አላገኘም" ሲሉ ተናግረዋል።

"እስከዛሬ ድረስ ውሃ የሚያነሳ ምርጫው ተጭበርብሯል የሚያሰኝ ማስረጃ አላገኘንም" ብለዋል ዊሊያም።

እስከዛሬ ሽንፈታቸውን አምነው ላልተቀበሉት ትራምፕ ይህ መልካም ዜና አይደለም ተብሏል።

ፕሬዝደንት ትራምፕ ከምርጫው በኋላ የድምፅ መጭበርበር አለ የሚል ማስረጃ የሌለው ክስ ሲያሰሙ ቆይተዋል።

ዐቃቤ ሕጉ መሰል ማጭበርበር የለም ባሉ በሰዓታት ልዩነት ትራምፕ ድምጼን ተሰርቄአለሁ የሚል መልዕክት ያላቸው ፅሁፎች ትዊተራቸው ላይ ለጥፈዋል።

ዊሊያም ባር፤ የአሜሪካ የፍትህ መስሪያ ቤትና የአገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስቴር ጉዳዩን ቢመርምሩም "እዚህ ግባ የሚባል ማስረጃ እንዳላገኙ" ሲሉ ተናግረዋል።

የፍትህ መስሪያ ቤቱ ቃል አቀባይ ከጠቅላይ ዐቃቤ ሕጉ መግለጫ በኋላ መሥሪያ ቤታችን አሁንም ቢሆን ምርመራውን ይቀጥላል ሲሉ ተሰምተዋል።

የትራምፕ ምርጫ ቅስቀሳ ቡድን ጠበቃ የሆኑት ሩዲ ጁሊያኒ እና ጄና ኤሊስ "ለጠቅላይ ዐቃቤ ሕጉ በክብር እጅ እንነሳለን፤ ነገር ግን ምርጫው በልሙጥ መንገድ መጭበርበሩን የሚያሳይ ምርመራ እንዳሉ እውቀቱ ያላቸውም" ብለዋል።

ይህንን እንካ ሰላንቲያ ተከትሎ ጉምቱው ዴሞክራት ቻክ ሹመር "ቀጣይ ተባራሪው ባለሥልጣን እንግዲያ ዊሊያም ባር ናቸው ማለት ነው" ሲሉ ተሳልቀዋል።

ለሳምንታት ምርጫው ተጭበርብሯል፤ እኔ በብዙ እጥፍ አሸንፊያለሁ እያሉ ሲወተውቱ ለነበሩት ትራምፕ ይህ ዜና መርዶ ነው ተብሏል።

ጠቅላይ ዐቃቤ ሕጉ ዊሊያም ባር የትራምፕ የቅርብ ሰው ናቸው።

የአሜሪካ ዜና አውታሮች ትራምፕ ጠቅላይ ዐቃቤ ሕጉና ኤፍቢአይ ምርጫው ተጭበርብሯል የሚለውን ሃሳባቸውን አለመደገፋቸው እንዳስቀየማቸው እየዘገቡ ነው።

ባር፤ የትራምፕ አስተዳደር የመጨረሻው መስዋዕት ሊሆኑ ይችላሉ እየተባሉ ነው።

እስካሁን በይፋ የምርጫውን ውጤት ያልተቀበሉት ትራምፕ፤ በትዊተር ገፃቸው ምርጫው ተጭበርብሯል የሚል በርካታ መልዕክቶችን ሲፅፉ ቆይተዋል።

ጆ ባይደን በይፋ ምርጫውን አሸንፈዋል ብለው ያወጁ የግዛት አስተዳዳሪዎችንም ወርፈዋል።

ምርጫውን ድል የነሱት ጆ ባይደን ከ50 ቀናት በኋላ የኃያሏን አገር መንበረ ሥልጣኑን ይረከባሉ ተብሎ ይጠበቃል።