ሁለት ሰዎችን የገደለው ታዳጊ በ2 ሚሊዮን ዶላር ዋስ ተለቀቀ

ታትሟል

ከጥቂት ወራት በፊት ጥቁር አሜሪካዊው ግለሰብ በፖሊስ መገደሉን ተከትሎ በተነሳ ተቃውሞ ላይ ሁለት ሰዎችን ገድሎ አንድ በማቁሰል የተጠረጠረው ታዳጊ ከእሥር በዋስ ተለቋል።

ካይል ቲትንሃውስ የተሰኘው የ17 ዓመት ነጭ ታዳጊ 2 ሚሊዮን ዶላር አስይዞ ነው የተለቀቀው ሲሉ የኬኖሻ ከተማ አስተዳዳሪዎች አስታውቀዋል።

ጄኮብ ብሌክ የተሰኘው ጥቁር አሜሪካዊ በነጭ ፖሊሶች በተደጋጋሚ በጥይት መመታቱን ተከትሎ በዊስኮንሲን ግዛት ተቃውሞ ተነስቶ ነበር።

በዚህ ተቃውሞ ላይ ታዳጊው ፖሊሶችን ደግፈው ሰልፍ ከወጡ መካከል ነበር።

የ17 ዓመቱ ታዳጊ በያዘው መሣሪያ ሶስት ሰዎች ላይ ተኩሷል ተብሎ ነው የተከሰሰው።

ተጠርጣሪው ኅዳር 4/2013 ፍርድ ቤት እንዲቀርብ ታዟል።

የኬኖሻ ከተማ ፍርድ ቤት የዋስ ገንዘቡ ከፍ እንዲል የተደረገው ተጠርጣሪው ጥፋተኛ ሆኖ ከተገኘ የዕድሜ ልክ እሥር ስለሚጠብቀው ነው ብሏል።

አልፎም ታዳጊው በአውሮፕላን እንዳይበር ስለሚፈልግ ነው ብሏል ፍርድ ቤቱ።

ከኢሊኖይ የመጣው ታዳጊ የ36 ዓመቱን ጆሴፍ ሮዘንባምና የ26 ዓመቱን አንተኒ ሁበር በመግደል እንዲሁም የ26 ዓመቱን ጌዥ በመግደል ሙከራ ወንጀል ተጠርጥሯል።

የታዳጊው ጠበቃ ማርክ ሪካርድስ ተጠርጣሪው ድርጊቱን የፈፀመው ራሱን ለመከላከል እንደሆነ የሚያሳይ ማስረጃ አለ ይላሉ።

ከሟቾቹ የአንዱ አባት የሆኑ ግለሰብ ታዳጊው ከሕግ በላይ እንደሆነ ስለሚያስብ የዋስትና ገንዘቡ ከፍ ሊል ይገባል ይላሉ።

ጉዳዩ በመገናኛ ብዙሃን ዘንድ ከፍተኛ ትኩረት አግኝቷል።

ታዳጊውን በገንዘብ ለመደገፍ የተቋቋመ ፈንድ ብዙ እርዳታ እያገኘ ነውም ተብሏል።

100 ሺህ ገደማ ሰዎች የሚኖሩባት ኬኖሻ ከተማ ብሌክ የተሰኘው ጥቁር አሜሪካዊ በፖሊስ ክፉኛ ከተመታ በኋላ ለቀናት ተቃውሞ አስተናግዳ ነበር።

በፖሊስ ጥይት በተደጋጋሚ የተመታው የሶስት ልጆች አባት የሆነው ብሌክ አሁን መንቀሳቀስ አይችልም።

ታዳጊው ከኢሊኖይ ወደ ኬኖሻ የመጣሁት በተቃውሞው ምክንያት ሱቆች እንዳይጎዱ ለመጠበቅ ነው ብሏል።

ካይል የተባለው ታዳጊ መንግሥት በኮሮናቫይረስ ምክንያት ለዜጎች የሰጠውን ድገሞ ገንዘብ ተጠቅሞ የጦር መሣሪያ እንደሸመተ ለዋሺንግተን ፖስት ጋዜጣ ተናግሯል።

ታዳጊው ተቃውሞውን በሚያሳዩ የተለያዩ ተንቀሳቃሽ ምስሎች ላይ መሣሪያውን አንግቦ ይታያል።

ታዳጊው ኢሊኖይ ከሚገኘው የእናቱ ቤቱ በፖሊስ ቁጥጥር ሥር እንዲውል ተደርጎ ነው ወደ ዊስኮንሲን የተወሰደው።